ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚገነባው ሙዚየም የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

 

አዲስ አበባ ሐምሌ 11/2015(ኢዜአ):- በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ገቢ በአሶሳ ከተማ ለሚገነባው ሙዚየም የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ናቸው።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስ፣ በክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢስሃቅ አብዱልቃድር፣ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ምስኪያ አብደላን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የሙዚየሙ ዲዛይን  የክልሉን አጠቃላይ ገጽታ በሚያሳይ መልኩ መዘጋጀቱንና በክልሉ ሊተዋወቁ የሚገባቸው በርካታ ታሪኮች፣ባህላዊ እሴቶች፣ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ሀብቶች እንዳሉ አቶ አሻድሊ ገልጸዋል።

ለሀብቶቹ መተዋወቅ የሙዚየሙ መገንባት ወሳኝ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

በክልሉ እስካሁን  ከመደመር ትውልድ መጽሐፍ ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ለክልሉ ይዞት የሚመጣው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከፍተኛ መሆኑን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።

የክልልሉ መንግስት ሙዚየሙ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በአጭር ጊዜ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም