ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ አጋር ተቋማት ለኢትዮጵያ ማዕድን ልማት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ሐምሌ 11/2015 (ኢዜአ):- ዓለም አቀፍ አጋር ተቋማት ለኢትዮጵያ ማዕድን ልማት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ጥሪ አቀረቡ።

የዩናይትድ ኪንግደም-አፍሪካ የሚኒስትሮች ፎረም በለንደን ተካሄዷል።

የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በፎረሙ ላይ የኢትዮጵያ የማዕድን ሃብትና የኢንቨስትመንት አማራጮች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ- ግብር እና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ እና አረንጓዴ ልማት ስራዎች አስመልክቶ የአገሪቷ ተሞክሮ ቀርቧል።


 

ኢትዮጵያ በሁሉም የልማት መስኮች የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን እየገነባች መሆኑንና  ከዚህም አንዱ የማዕድን ዘርፍ እንደሆነ ኢንጂነር ሀብታሙ ገልጸዋል።

መንግስት ለማዕድን ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልጸው መዋዕለ ንዋያቸውን በዘርፉ ለሚያውሉ ባለሃብቶች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የዘርፉ ተዋናዮች የኢትዮጵያን የማዕድን ዘርፍ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሰው ኃይል ልማት፣መሰረተ ልማት እና ፋይናንስ እንዲደግፉ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሱልጣን ወሊ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፏን ለማሳደግ ማስተር ፕላንን ማዘጋጀት ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የልማት አጋር ተቋማት ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፉ ለምታከናውናቸው የልማት ተግባራት ድጋፍ እንዲያደርጉ ገልጸዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም-አፍሪካ የሚኒስትሮች ፎረም የአፍሪካ አገራት በመሰረተ ልማት፣ በማዕድን እና ኢነርጂ ዘርፎች እያከናወኑ ያለውን የካርቦን ቅነሳ ስራ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

የአፍሪካ አገራት እና የእንግሊዝ መንግስት የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ የሚያስችል ምቹ የንግድ ከባቢ መፍጠርን ማዕከል ያደረጉ ምርጥ የፖሊሲ ተሞክሮዎች ቀርበውበታል።

የአፍሪካ አገራት ሚኒስትሮችም የልምምድ ልውውጥ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም