ዳያስፖራው በአገራዊ የልማት ሂደት ውስጥ እያበረከታቸው ያሉ በጎ አስተዋጽኦችን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው በአገራዊ የልማት ሂደት ውስጥ እያበረከታቸው ያሉ በጎ አስተዋጽኦችን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ
አዲስ አበባ ሐምሌ 11/2015(ኢዜአ)፦ዳያስፖራው በአገራዊ የልማት ሂደት ውስጥ እያበረከታቸው ያሉ በጎ አስተዋጽኦችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር ዘላቂ አገራዊ ትስስርና ተሳትፎን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ እና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ እና የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ዳያስፖራው ለአገሩ ጥብቅና በመቆምና ድጋፍ በመስጠት፣ የአገር ድምጽ በመሆንና ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሻራውን በማስቀመጥ ላደረገው አበርክቶ ምስጋና አቅርበው ጥረቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ዳያስፖራው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነጻነት በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ እንዲሁም በቢዝነስ እድሎች ላይ በስፋት መሳተፍ ይጠበቅበታል ሲሉም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ በበኩላቸው ዳያስፖራው የአገሩ አምባሳደር በመሆን በገጽታ ግንባታ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህልና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ያደረገው አስተዋጽኦ ዘመን ተሻጋሪ ነው ብለዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘላቂ አገራዊ ትስስርና ተሳትፎን ለማጠናከር በአዳዲስ እሳቤዎች መምራት እንደሚያስፈልግ ገልጸው ተቋሙ ለቀጣይ ጊዜ የሚሆኑ አዳዲስ አስተሳሰቦችን፣ አሰራሮችንና ፓኬጆችን ለመተግበር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ዳያስፖራው በአገራዊ ልማት፣ በገጽታ ግንባታ፣ በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተሳትፎውን ማሳደግ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች አገራዊና ወቅታዊ አጀንዳዎችን፣ የመረጃ ተደራሽነት፣ በኢንቨስትመንት ተሳትፎ ላይ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶች፣ የዳያስፖራ መብቶች፣ የአገልግሎት አሰጣጥንና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄና ሀሳቦችን አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
እንደ አገር ያጋጠሙትን ፈተናዎች በውይይትና በመመካከር መፍታት እንዲቻል አገራዊ የምክክር ኮሚሽን እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱንና የመልሶ ግንባታ ስራዎችን ዳያስፖራው መከታተል፣ ማወቅና መደገፍ እንደሚገባው ተገልጿል።