ቀጥታ፡

በኢትዮጵያውያን አረንጓዴ ታሪክ ተሠርቷል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ሐምሌ 11/2015 (ኢዜአ) ፦ 500 ሚልዮን ዛፎችን በመትከል የራሳችንን ሪከርድ እንድንሰብር የቀረበውን ጥሪ ተቀብላችሁ የወጣችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል፤ አረንጓዴ ታሪክ ሠርታችኋል፤ አረንጓዴ ታሪክ ጽፋችኋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ “የተዛባ አየር፣ የተራቆተ ምድር ለትውልድ አናወርስም ብላችሁ፤ ጎሕ ሳይቀድ ወደ ተራሮችና ሸለቆዎች፣ ወደ ሜዳዎችና ሸንተረሮች ተሠማርታችሁ 566 ሚልዮን ዛፎች ተክላችኋል። ሪከርዳችሁን ሰብራችኋል” ብለዋል።


 

በሁሉም ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ዛፎች ተተክለዋል፤ ከ9 ሺ በላይ የተለዩ ቦታዎች ተዘጋጅተው እንደነበር ገልጸው፤ ከ3 ሺህ 600 በላይ የሚዲያ ባለሞያዎች በመላ ሀገሪቱ ተሠማርተው እንደነበር ጠቅሰዋል።

የቴሌና የግብርና ባለሞያዎች የመረጃ አያያዙ ዘመናዊ እንዲሆን መስራታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ታክሲዎች ነጻ ትራንስፖርት ለችግኝ ተካዮች መስጠታቸውንም ተናግረዋል።


 

ሕጻናት፣ እናቶች፣ አባቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ በነቂስ ወጥተው ችግኝ መትከላቸውን ገልጸው፤ በኢትዮጵያውያን ዛሬ አረንጓዴ ታሪክ ተሠርቷል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ኢትዮጵያውያን ከተባበርን የማንሰብረው ሪከርድ የለም ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም