ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ዛሬ በተካሄደው አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለተሳተፉ ዜጎች ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት ተሰጥቷል - የሚኒባስ ታክሲና ሃይገር ባሶች ማኅበራት ጥምር የጋራ ኮሚቴ 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10/2015(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ዛሬ በተካሄደው አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ ለተሳተፉ ዜጎች ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠታቸውን የሚኒባስ ታክሲና ሃይገር ባሶች ማኅበራት ጥምር የጋራ ኮሚቴ ገለጸ። 

በአዲስ አበባ ከማለዳው ጀምሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተካሄደ ሲሆን በርካታ ዜጎች ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የ13 ሚኒባስ ታክሲ እና የ3 ሃይገር ባስ ማኅበራት የጋራ ጥምር ኮሚቴ አስተባባሪ አያሌው ስዩም ለኢዜአ እንደገለጹት ዛሬ በተካሄደው አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ የታክሲ ማኅበረሰቡ ችግኞችን በመትከል አገራዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል።

ከዚህ ጎን ለጎን አዲስ አበባ ዛሬ በተካሄደው አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለተሳተፉ ዜጎች ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በአራት ተርሚናሎች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠታቸውንም ነው የገለጹት።  

ይህን በማድረጋችን ትልቅ ደስታና ኩራት ተሰምቶናል ያሉት አስተባባሪው ችግኝ ለሚተክሉ ዜጎች ሲቀርብ የነበረው ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት ስኬታማ እንደነበር ተናግረዋል። 

በቀጣይም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ያላቸውን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩ ጠቁመው መሰል አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ በመሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት የበለጠ ለመወጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በየካ ክፍለ ከተማ የሕዝብና ጭነት ትራንስፖርት ድልድልና ሥምሪት ቡድን መሪ ወጣት ነብዩ እሸቱ በበኩሉ የዓለም ችግር የሆነው አየር ንብረት ለውጥን ለመግታት በሚደረገው አገራዊ ጥሪ ላይ መሳተፍ ትልቅ ደስታ ይሰጣል ብሏል።

በቀጣይም ተሳትፎውን አጠናክሮ በመቀጠል የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እንደሚሰራ ተናግሯል። 

የሕዳሴ ተራ አስከባሪዎች ማኅብር ሊቀ-መንበር ወጣት ትንቢተ አበበ በበኩሉ ችግኝ መትከል ብቻ ግብ ባለመሆኑ ተከታትሎ እንክብካቤ ማድረግ ወሳኝ ነው ብሏል።

 

  

 

            

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም