ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያን ከተባበርን የማናሳካው ልማት እንደማይኖር በተግባር እያሳየን ነው - አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ/ ሠመራ/  አሶሳ/ ጅግጅጋ ሐምሌ 10 ቀን 2015 (ኢዜአ)፡-  ኢትዮጵያዊያን ከተባበርን  የማንሻገረው ችግርና የማናሳካው  ልማት እንደማይኖር በተግባር እያሳየን ነው ሲሉ  የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በበኩላቸው፤ ችግኞችን መትከል የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም ያግዘናል ብለዋል።

በሌላ በኩል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዛሬ የተካሄደው የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ዘመቻ አንድነትን በሚያጠናክር መልክ መካሄዱ ተገልጿል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድሩ  አቶ ኡሞድ ኡጁሉ  የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራን ውሎ አስመልክተው እንደገለፁት፤  በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በርካታ ህዝብ በመውጣት  የአንድ ጀምበሩን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በስኬት ማጠናቀቅ ችሏል።

እኛ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት  በትብብርና በቅንጅት ከሰራን የማንሻገርው ችግርና የማናሳካው  ልማት እንደማይኖር በተግባር እያሳየን ነው  ብለዋል።

የዚህም ዋነኛ ማሳያው ህዝቡ  በአንድነት በመነሳት ዛሬ  በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ላይ ያስመዘገበው ውጤት እንደሚጠቀስ ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለዕቅዱ ስኬታማነት መላው  የክልሉ ህዝብና የመገናኛ ብዙሃን  ባለሙያዎች ላደረጉት ቀና ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ  በሰጡት መግለጫ ችግኞችን መትከል የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም ያግዘናል" ብለዋል።


 

ርዕሰ መስተዳደሩ ይህንን የገለጹት ዛሬ  በአንድ ጀንበር  የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር በክልሉ ገቢ ረሱ ዞን በዱለቻ ወረዳ ዱራፍሌ ቀበሌ በተካሄደበት ወቅት ነው።

በደን መመናመን ምክንያት በአካባቢያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በተለይም በአርብቶአደር አካባቢ እየደረሰ ያለውና የድርቅ ተጋላጭነት ከመቀነስ አኳያ የአረንጓዴ አሻራ ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በዛሬው  መርሃ ግብራችን እኛ ኢትዮጵያውያን ለዓለም ትብብራችን እና አንድነታችንን በተግባር አሳይተናል ሲሉ ተናግረዋል።

የምንተክላቸው ችግኞች የነገ ውበት መሆናቸውን ተገንዝበን እንዲፀድቁ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀው፤ ለዛሬው መረሃ ግብር መሣካት አሰተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ አመስግነዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዛሬ የተካሄደው የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ዘመቻ  አንድነትን በሚያጠናክር መልክ መካሄዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ  ሃለፊ አቶ ባበክር ከለፋ አስታውቀዋል።


 

ሃላፊው ማምሻውን  በሰጡት መግለጫ በክልሉ የዛሬው የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ዘመቻ ስኬታማ  መሆኑን ገልጸዋል። 

የክልሉ  መንግስት ሠራተኛውና አርሶ አደሮች ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው በዘመቻው በንቃት መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ ችግኝ ተከላው ዓላማውን ከማሳካቱም በላይ የህብረተሰቡን ሀገራዊ አንድነት በሚያጠናክር መልኩ መከናወኑን አስታውቀዋል።

እንዲሁም የሥራ ባህላችንን በማሻሻል ያለውን ፋይዳ የጎላ ነው ያሉት ሃላፊው፤ የክልሉ ህብረተሰብ  በችግኝ ተከላው ያሳየውን ርብርብ በዘላቂ እንክብካቤ እንዲደረግም አቶ ባበክር ጠይቀዋል። 

በሌላ በኩል ለድጋፍና ክትትል በሶማሌ ክልል ከተሰማሩት ከፍተኛ የፌዴራል መንግስት አመራሮች መካከል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ  በስፍራው እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል የተከናወኑ  የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ደርቆ የነበሩ የውሃ አካላት መልሶ እንዲለመልሙ አስችሏል።  


 

ሀገራችን ያሏት አስራ ሁለት ተፋሰሶችና ቀንሶ የነበሩ የውሃ አካላት   በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተከናወነው ስራ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ነዋሪዎች ስለ አረንጓዴ አሻራ በቂ ግንዛቤ እየተፈጠረላቸው በልማቱ የሚያደርጉት ተሳትፎ እየጎለበተ መምጣቱን ጠቁመዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም