ህይወታችንን በተሻለ ሁኔታ ለማስቀጠል አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩን አጠናክረን እናስቀጥላለን - - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ - ኢዜአ አማርኛ
ህይወታችንን በተሻለ ሁኔታ ለማስቀጠል አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩን አጠናክረን እናስቀጥላለን - - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ
ሀዋሳ ሐምሌ 10/ 2015 (ኢዜአ)''ህይወታችንን በተሻለ ሁኔታ ለማስቀጠል አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩን አጠናክረን እናስቀጥላለን'' ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አሳሰቡ።
''ነገን ዛሬ እንትከል'' በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ከክልሉና ከፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በሀዋሳ ሀይቅ ዳር ችግኝ ተክለዋል።
በዚሁ ወቅት ርዕሰ መስተዳድር ደስታ እንዳሉት ''ችግኝ የምንተክለው ለማንም አይደለም፣ የተከልነው ዛፍ ራሱ አየር፣ ምግብና ቤት ነው'' ብለዋል።
''ችግኝ መትከል የህይወት ዋስትና ስለሆነ ህይወታችንን በተሻለ ሁኔታ ለማስቀጠል አረንጓዴ አሻራችንን አጠናክረን እናስቀጥላለን ሲሉም'' መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዚህም እንቅስቃሴ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን ለማጠናከር ስለሚያስችል መላው የክልሉ ህዝብ በተከላው ለማሳተፍ ሁኔታዎች መመቻታቸውን አስታውቀዋል።
ሁሉም የክልሉ ነዋሪ የቻለውን ያህል ችግኝ በመትከል ኃላፊነቱን እንዲወጣ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ በጋራ ለመበልጸግ ሁሉም ያላሳለሰ ጥረት ማድረግ አለበት።
በሀዋሳ ችግኝ ተከላ መርሀ ግበር ላይ የተሳተፉት የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው በክልሉ የክረምት ስራንና አጠቃላይ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግበርን ለማስተባበር በክልሉ ለ11 ቀናት ቆይታ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
''ለአረንጓዴ ልማት ስኬታማነት መትከል ብቻ ሳይሆን በመንከባከብ ላይ ሊታስብበት ይገባል'' ያሉት ሚኒስትሯ፣ የተጀመረው ስራ መጠናከር አለበት ብለዋል።
ካለምንም ልዩነት፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በመሆኑ ብቻ አሻራውን በማኖር ተሷትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ሀዋሳ ሀይቅ ዳር እየተካሄደ ባለው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞችና አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶች አደረጃጀቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በነቂስ ወጥተው በመሳተፍ ላይ ናቸው።