ቀጥታ፡

የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሠራተኞች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አካሄዱ

 

አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2015(ኢዜአ)፦የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሠራተኞች "ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ በመትከል አሳልፈዋል።

የፕሮጀክቱ የአካባቢና ማህበራዊ ዕቅድ ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው ደሳለኝ እንደገለፁት በዕለቱ የምግብነት ጠቀሜታ ያላቸውን የፍራፍሬ ችግኞች መትከል ተችሏል።

ፕሮጀክቱ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ከተጀመረበት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የራሱን የችግኝ ማፍያ ጣቢያ በማቋቋም በየዓመቱ በርካታ ችግኞች መትከሉን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ግዛቸው ገለፃ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ዛፎችን በመትከል የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር ከመጠበቅ ባሻገር በፕሮጀክት ሳይት የሚገኙ ሠራተኞች ከፍራፍሬ ምርቶች እና ከጓሮ አትክልቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።

ፕሮጀክቱ በዛሬው ዕለት ከ500 በላይ የአቮካዶ እና የማንጎ ችግኞች መትከሉንም ነው ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት።

በተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጭ እና አማካሪ ድርጅት ሠራተኞች በንቃት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም