ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከህፃን እስከ አዋቂ እየተሳተፉበት የሁሉም አደራ ሆኖ ቀጥሏል

አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከህፃን እስከ አዋቂ እየተሳተፉበት የሁሉም አደራ ሆኖ ቀጥሏል።

በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ25 ቢሊዬን በላይ ችግኞችን በመትከል የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከነበረበት ሶስት በመቶ ወደ 15 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡

የአረንጓዴ ልማቱ ተጠናክሮ ቀጥሎ ዘንድሮም ሁለተኛው መእራፍ ተጀምሮ የዚሁ መርሃ ግብር አካል የሆነውም የአንድ ጀምበር የ500 ሚሊየን ችግኝ ተከላ በመከናወን ላይ ይገኛል።

በዚሁ ሁነት ላይ ከህፃናት እስከ አዋቂ፤ ከአርሶ አደር እስከ ነጋዴ፤ ተማሪዎች ምሁራንና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች በነቂስ ተሳትፈውበታል።

በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ አይ ሲ ቲ ፓርክ ዝናቡን ተቋቁመው ጠዋት 12 ሰዓት ጀምሮ የወጡ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ባለሙያዎች፣ የጸጥታ ኃይሎች ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡

በዚህ ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሶስት ዓመቱ ህፃን ዳዊት ታደሰ በመሳተፍ ነገን ዛሬ መትከል ችሏል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ የደብረ በረከት ወይን አንባ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ መጋቢ ኃይማኖት የማነብርሃን ዕንባቆም፤ የእጽዋት ልማት ህይወትን ማስቀጠል በመሆኑ ችግኞችን መትከላችን ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም በአረንጓዴ ልማት ከጥንት እስካሁንም ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ ውጤታማ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

በዛሬው እለት አሻራቸውን ያኖሩት የየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪው ካሱ አያኖ፤ ዛፍ መትከል ለልጆቻችን የምናስተላልፈው ሀብት ቅርስ እና ህይወት በመሆኑ አሻራችንን ማኖራችን ይቀጥላል ብለዋል።  

"ዛፎች የሚሰጡንን ንጹህ አየር ዘር ሀይማኖት ቀለም ሳይመርጡ ለሁላችንም እኩል ነው" የሚሉት መጋቢ ኃይማኖት የማነብርሃን ዕንባቆም ኢትዮጵያውያንም ከዚህ በመማር ችግኞችን በአንድነት እንደተከልን በአንድነት መንከባከብ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የእስልምና ኃይማኖት አባት የሆኑት ሼህ የሱፍ መሀመድ፤ በእምነታችን መሰረት "ዛሬ የመጨረሻ ቀን ነው ቢባል እንኳን አንድ ችግኝ ተክላችሁ እለፉ" ይላል ብለዋል።

በነብያችን አስተምህሮም "አንድ ችግኝ እንኳን ቢሆን ያለ ፋይዳ አይቆረጥም" መትከልና መንከባከብም እንደሚገባ ስለነገሩን በዚሁ መሰረት ስራችን ይቀጥላል ነው ያሉት።

በየካ ክፍለ ከተማ የሀገር ሽማግሌ ክንፈ ተፈሪ የችግኝ ተከላ አላማው ለአገር ህልውና መቀጠል በመሆኑ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

"እኔ ችግኝ የተከልኩት ከማላውቃቸው ሰዎች ጋር ነው፤ የአንድነትና የትብብር መንፈሱ ግሩም ነው፤ አስደንቆኛል ቀጣይነትም ሊኖረው ይገባል" በማለት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

የኢትዮጵያውያን የዛሬው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አንድነት፣ ትብብርና አብሮነት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

በፌደራል ፖሊስ ፎረንሲክ የDNA ምርምራ ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ወንድማገኝ ጸጋዬ እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ሳጅን አለምነሽ አለማየሁ፤ ፖሊስ ዋና ሥራው ህግ በማስከበር የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ቢሆንም በማህበራዊ አገልግሎቶችም የነቃ ተሳትፎ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማድረግ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፤ ችግኝ መትከል ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የሥራ ዕድል በመፍጠር ወንጀልን መቀነስ ያስችላል ብለዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የእዕዋት ተባይ መከላከል ባለሙያ ጌጤነሽ ስምኦን፤ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ችግኞችን መትከልና በዘላቂነት መንከባከብ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዘውዲቱ ሆስፒታል ሃኪም ሲስተር የወርቅውሃ ችግኞች ኦክስችንን በማምረት የሰው ልጆችን ሥርዓተ ህይወት የተቃና የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉም መትከል አለበት ብለዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም