የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት የዜጎች የወደፊት ተስፋና የአገር ህልውና መሰረት በመሆኑ ለስኬቱ የጋራ ጥረታችን ይቀጥላል- የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት የዜጎች የወደፊት ተስፋና የአገር ህልውና መሰረት በመሆኑ ለስኬቱ የጋራ ጥረታችን ይቀጥላል- የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ
አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት የዜጎች የወደፊት ተስፋና የአገር ህልውና መሰረት በመሆኑ ለስኬቱ የጋራ ጥረታችን ይቀጥላል ሲሉ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ተናገሩ።
በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ መስከረም ደበበ፤ የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ፣ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና የከተማዋ ነዋሪዎች በሸገር ከተማ ኖኖ ወረዳ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
በእለቱ አሻራቸውን ያኖሩት ኃላፊዋ፤ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የቀረበውን ጥሪ በመቀበል ሁላችንም አሻራችንን አኑረናል ብለዋል።
በቀጣይም ችግኞችን እየተከልንና እየተንከባከበን አገራችንን አረንጓዴ ከማድረግ በተጨማሪ የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት የዜጎች የወደፊት ተስፋና የአገር ህልውና መሰረት በመሆኑ ለስኬቱ የጋራ ጥረታችን ይቀጥላል ብለዋል።
የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ፤ ለዜጎች የተመቸች አገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የሸገር ከተማ ነዋሪዎች ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በዛሬው እለትም በአገር አቀፍ ደረጃ የቀረበውን ጥሪ በመቀበል በትብብርና አብሮነት አሻራችንን አኑረናል ብለዋል።
በሸገር ከተማ 70 በመቶው ለአረንጓዴ እና ለግብርና ልማት መዋል የሚችል በመሆኑ በሁሉም ዘርፍ ውጤት ለማምጣት እየሰራን እንገኛለንም ነው ያሉት።
የሁለተኛው ምእራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ቀደም ብሎ የተጀመረ ሲሆን የዚሁ አካል የሆነው አገር አቀፍ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላም በመከናወን ላይ ይገኛል።