ቀጥታ፡

በችግኝ ተከላ ወቅት የሚታየው ተነሳሽነትና ርብርብ ችግኞቹን በመንከባከብም ሊደገም ይገባል-የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ

አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2015(ኢዜአ)፡- በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በችግኝ ተከላ ወቅት የሚታየው ተነሳሽነትና ርብርብ ችግኞቹን በመንከባከብም ሊደገም እንደሚገባ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን አመራርና ሠራተኞች አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ አሻራ ከራሷም ባሻገር ለዓለምም ጭምር የሚተርፍ ነው።

በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ እየተጎዳ ላለው ዓለም ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል መርሃ ግብርም ኢትዮጵያ የራሷን ሪከርድ የምታሻሽልበትና አዲስ ታሪክ የምትጽፍበት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ለመጪው ትውልድ አረንጓዴ የለበሰች አገር ለማስረከብ አስተዋጽኦ እንዳለው የተናገሩት ሚኒስትሯ ችግኞችን በመትከል በኩል የታየው ተነሳሸነት ችግኞቹን በመንከባከብ መደገም አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በበኩላቸው ቅርሶችን ጠብቀን ለትውልዱ እንደምናስተላልፈው ሁሉ ተፈጥሮንም ጠብቀን ለማስተላለፍ ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም