የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የኃይል ማመንጫ ግድቦች ደህንነት ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የኃይል ማመንጫ ግድቦች ደህንነት ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2015 (ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ደህንነት ለማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል "ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል መሪ ሀሳብ በሰበታ ከተማ 2 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፊያ ጣቢያ ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ መርኃ-ግብር አከናውኗል።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ በመርሐ-ግብሩ ላይ እንደገለጹት የችግኝ ተከላው የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ደህንነት ለማስጠበቅ ፋይዳው የጎላ ነው።
የችግኝ ተከላው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ከደለል ለመከላከል እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
የተቋሙ የሰው ኃይል፣ የፋይናንስ፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ዘርፎች ሥራ አስፈፃሚዎች በበኩላቸው የችግኝ ተከላውን ጠቀሜታ በተመለከተ አስተያየት ሰጥተዋል።
ሥራ አስፈጻሚዎቹ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ተቋሙ ለሀገር ዕድገትና ለአህጉራዊ ትስስር መሰረት የሚሆን አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እንደሚያግዘው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢኮኖሚን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ተቋሙ ግንባር ቀደም ሚና ይጫወታል ብለዋል።
በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉ ሠራተኞችም ተቋሙንና ሀገርን በሚለውጥ መርሐ-ግብር ላይ በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ገልፀው የተከሏቸውን ችግኞች እንደሚንከባከቡ መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል።