ቀጥታ፡

ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በዘላቂነት መንከባከብ ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል-አቶ ረሻድ ከማል

አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2015 (ኢዜአ) ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በዘላቂነት መንከባከብ ላይ ሁሉም ትኩረት አድርጎ ሊሰራ ይገባል ሲሉ  የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል ገለጹ።

ዛሬ ማለዳ የተጀመረው የአንድ ጀምበር የ500 ሚሊየን ችግኞች ተከላ መርሃ-ግብር "ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናልብስ፤ ነገን እንትከል፤ ታሪክን እንትከል!" በሚል መሪ ቃል  በተጠናከረ  መልኩ  ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አመራርና ሠራተኞች በጉለሌ እጽዋት ማዕከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

የቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል በዚሁ ወቅት "የአረንጓዴ አሻራ የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ" ወሳኝ ሥራ መሆኑን ገልፀዋል።

እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአካባቢን ሥነ-ምህዳር በማስተካከል ያልተዛባ አየር ንብረት እንዲኖር እና ንጹህ አየር ለማግኘትም እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ የአየር ንብረትን ለመቋቋም የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን ማሳያ ነው ሲሉም አክለዋል።

ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት መንከባከብ ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። 

ኮርፖሬሽኑ በዚህ ረገድ ከዚህ ቀደም የተከላቸውን ችግኞች በመንከባከብ ረገድ ከፍተኛ ሥራ መሥራቱን አንስተዋል። 

የቀረበውን አገራዊ ጥሪ በቅን ልቦና በመውሰድ ለተግባራዊነቱ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተፈራ በቀለ በበኩላቸው፤ ሕብረተሰቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግኝ የመትከል ባህሉ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።


 

እየመጣ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ስጋትን ለመከላከል እንዲሁም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደዚህ ዓይነት ባህሎችን አጠናክሮ በመቀጠል የአገሪቱ ልማትና እድገት ማፋጠን ይገባል ሲሉም አክለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም