ቀጥታ፡

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የችግኞችን የፅድቀት መጠን ለማሳደግ ይስራል-ግብርና መምሪያው

እንጅባራ ሐምሌ 10/2015 (ኢዜአ):- በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በክረምት የሚተከሉ ችግኞችን የመፅደቅ መጠን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ የአስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በአስተዳደሩ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር "ቢተርያ" ተብሎ በሚጠራው ተራራ ላይ ተከናውኗል።

የመምሪው ኃላፊ ዶክተር ታደሰ አስፋው እንዳሉት በዞኑ ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ በተተከሉ ችግኞች ጥሩ ውጤት እየተገኘ መጥቷል።

የዞኑ የደን ሽፋን ከማደጉ ባለፈ ሕብረተሰቡ ደንን እንደ ሀብት ይዞ የመጠበቅና የመንከባከብ ባህሉ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው ይህንን ልምድ ለማጠናከርም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው መርሐ-ግብር የአፈር ለምነትንና የአካባቢ ስነ-ምህዳር ለመጠበቅ ከሚያስችሉ የደን ችግኞች በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች እየተተከሉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞች ፀድቀው ለውጤት እንዲበቁ ያለፈውን ልምድ በመቀመር የእንክብካቤና የጥበቃ ሥራው በልዩ ሁኔታ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በችግኝ ተከላው የተሳተፉት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፓሊስ አባል ሻምበል አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር መላኩ መርሻ እንደገለጹት፣ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ለፅድቀታቸው በትኩረት መስራት ያስፈልጋል።

"ፌደራል ፓሊስ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ የሚያስፈልገውን እንክብካቤ ከማድረግ ባለፈ ያለአግባብ እንዳይቆረጡም ጥበቃ ያደርጋል" ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም