በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር የታየው የቅንጅትና የትብብር ስራ የትኛውንም የልማት እቅድ ማሳካት እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ ነው- ዶክተር ለገሰ ቱሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር የታየው የቅንጅትና የትብብር ስራ የትኛውንም የልማት እቅድ ማሳካት እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ ነው- ዶክተር ለገሰ ቱሉ
አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2015(ኢዜአ)፦ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ላይ የታየው የቅንጅትና የትብብር ስራ የትኛውንም የልማት እቅድ ማሳካት እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመላው ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀምበር የ500 ሚሊዮን የችግኝ ተከላ ጥሪ መሰረት በመከናወን ላይ ይገኛል።
በዚሁ መርሐ-ግብር ላይ በመገኘት አሻራቸውን ያኖሩት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፤ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከችግኝ መትከል በላይ የሕልውና ጉዳይ እና ድርቅን በመከላከልና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።
በመሆኑም በአንድ ጀምበር የ500 ሚሊዮን የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ላይ የታየው የቅንጅትና የትብብር ስራ የትኛውንም የልማት እቅድ ማሳካት እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የቀጣይ ዓመት እቅድም በአረንጓዴ አሻራና በሰብል ልማት ጥሩ ውጤት ማስመዝግብ መሆኑን ጠቅሰው ለዚሁ እቅድ ስኬት በህዝቡ ዘንድ የታየው ተሳትፎ የሚያስደንቅ ነው ሲሉም ገልጸውታል።
በመሆኑም በቀጣይ ዓመት የልማት እቅዶቻችን በማሳካት የሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን አጠናክረን የምንቀጥልበት ይሆናል ነው ያሉት ዶክተር ለገሰ።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የታየው ትብብርና ቅንጅትም በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና ሌሎችም ተግባራት እቅዶችን ማሳካት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ፤ ኢትዮጵያውያን አገርን በማስከበር ሂደት ያሳዩትን አንድነትና ትብብር በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መድገማቸውን ገልጸዋል።
በመርሐ-ግብሩ ዜጎች ያሳዩት ቁርጠኝነትም የኢትዮጵያ ብልጽግና አይቀሬ መሆኑን ያመላከተ ነው ብለዋል።