የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2015(ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩት አመራሮች እና ሰራተኞች በአንድ ቀን 500 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል በተያዘው አገራዊ መርሐ-ግብር አረንጓዴ አሻራቸውን በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ ዞን ዲባንዲባ ቀበሌ በክላስተር እየለማ በሚገኝ የእርሻ ማሳ ላይ አኑረዋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ይፍሩ ታፈሰ እንዳሉት የችግኝ ተከላው የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ያም ብቻ ሳይሆን አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአፈር ለምነትን በመጠበቅና የተራቆተውን የአካባቢ ስነ-ምህዳርን በማስተካከል ረገድ ያለው ጠቀሜታ ጉልህ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር እየተተከሉ የሚገኙት የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ለማህበረሰቡ የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ የሚያግዙ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም እንደሚሆን አመልክተዋል።
መርሐ-ግብሩ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶቹን በቀጣይ ለውጭ ገበያ በማቅረብ አርሶ አደሮቹን ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል ነው ያሉት ዶክተር ይፍሩ።
ይህም እውን እንዲሆን በኢትዮጵያ በየትኛውም ስፍራ የተተከሉ ችግኞች እንዲፀድቁ መከታተልና መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።