ቀጥታ፡

አካል ጉዳተኛነት ታሪክ ከመትከል አያግደንም - አካል ጉዳተኞች

መቱ / ጅግጅጋ ሐምሌ 10/2015(ኢዜአ) አካል ጉዳተኛነት ታሪክ ከመትከል አያግደንም  ሲሉ የአካል ጉዳተኞች ተናገሩ።

በአንድ ጀምበር የ500 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሐ-ግብር በመላው የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተካሄደ ነው።

በመርሐ-ግብሩ ላይ በተለያየ እድሜ ደረጃ የሚገኙ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በኢሉባቦር ዞን እየተሳተፉ ካሉ ዜጎች መካከል በዞኑ የሁሩሙ ወረዳ ዩቢ ዶላ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ሙሉጌታ ታደሰ ይገኙበታል።

አቶ ሙሉጌታ መራመድ የማይችሉ አካል ጉዳተኛ ናቸው። 

“አረንጓዴ አሻራ ለትውልድ ታስቦ የሚሰራ በመሆኑ አካል ጉዳተኝነቴ የልጅቼ የነገ ስንቅ የሆነውን ችግኝ ከመትከል አያግደኝም" ብለዋል።

መርሐ-ግብሩ ሁሉንም እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

''ልክ ለልጆቼ የማደርገውን እንክብካቤና ክትትል ለተከልኳቸው ችግኞች በማድረግ ችግኞቹ እንዲጸድቁ እተጋለሁ'' ብለዋል።
 
በችግኝ ተከላ መርሐ-ግብሩ የተሳተፉ ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ  የሕዝቡን አንድነት ያጠናክራል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ባለው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ላይ እየተሳተፉ ካሉት የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት የአራተኛ ዓመት ተማሪ መሐመድ አብዲላሂ አደን አንዱ ነው።
 
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ  አህመድ የቀረበውን አገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት እየተካፈለ መሆኑን ይገልጻል።
 
ዛሬ ካራማራ ተራራ ላይ በመውጣት በርካታ ችግኞችን በመትከል የራሱን አሻራ መኖር መቻሉ ልዩ ደስታ እንደፈጠረበት ተናግሯል። 
 
“አካል ጉዳተኛ ብሆንም ታሪክ ለመትከልና ኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ ለማልበስ ከመሳተፍ አላገደኝም" ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም