ቀጥታ፡

ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ በአገር ልማት ላይ የራሱን ዐሻራ ማኖሩን ይቀጥላል - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ-ሚካኤል

አዲስ አበባ  ሐምሌ 10/2015(ኢዜአ) ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ በአገር ልማት ላይ የራሱን ዐሻራ ማኖሩን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ-ሚካኤል የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት ተናገሩ።

የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮችና አባላቱ ዛሬ እየተከናወነ ባለው የ500 ሚሊየን የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በኮልፌ ክፍለ ከተማ ቤተል ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የአረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።

በእለቱ አሻራቸውን ያኖሩ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ-ሚካኤል፤ የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት የኢትዮጵያን የአየር ሚዛን በመጠበቅ የሚኖራቸውን ፋይዳ ከግምት በማስገባት የተተከሉ ችግኞችን እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ፌደራል ፖሊስ የአገርን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት ከመወጣት ባለፈ በአገራዊ የልማት ስራዎችም የነቃ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ በአገር ልማት ላይ የራሱን ዐሻራ ማኖሩን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ፤ አረንጓዴ ዐሻራ ልማት የአየር ንብረት ሚዛንን በመጠበቅ ድህነትን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የላቀ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

የፖሊስ አባላትም የህዝብን ሰላምና ጸጥታ ከማስጠበቅ በተጓዳኝ በተለያዩ አገራዊ የልማት ስራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዛሬው እለት በአገር አቀፍ ደረጃ በተከናወነው የአረንጓዴ ልማት የላቀ ተሳትፎ በማድረግ ጭምር አሻራቸውን ማኖራቸውን ገልጸዋል።

የፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፋንታ፤ ኢትዮጵዊያን አገራቸውን አረንጓዴ ለማልበስ ከሚያደርጉት ርብርብ ጎን ለጎን ሰላምና ደህንነትን በመትከል አብሮነትን ማስቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ለአረንጓዴ ዐሻራ ያሳዩትን አንድነትም ለአብሮነት፣ ፍቅርና የጋራ ተጠቃሚነት ማዋል አለባቸው ነው ያሉት።  

በመርሃ ግብሩ ላይ ከተሳተፉት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖሊስ አባላት ለአገርና ህዝብ ዘብ ከመሆን በተጨማሪ በዚህ አገራዊ የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም አሻራቸውን በማኖራቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአንድ ጀምበር የ500 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ላይ ኢትዮጵያዊያን የላቀ ተሳትፎ በማድረግ የራሳቸውን ክብረ ወሰን እንዲያሻሽሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በዛሬው እለትም "ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል መርህ የአንድ ጀምበር አገር አቀፍ የችግኝ ተከላ በመከናወን ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም