የዛሬ ቀን ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ ታሪክ የሚሰራበት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
የዛሬ ቀን ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ ታሪክ የሚሰራበት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2015(ኢዜአ)፡-የዛሬ ቀን ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ ታሪክ የሚሰራበትና የይቻላል ውጤት የምናይበት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር በጉለሌ እጽዋት ማዕከል ተገኝተው አረንጓዴ አሻራቸውን ባኖሩበት ወቅት ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ዕለቱ ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ ታሪክ እየተሰራበት ያለ ቀን መሆኑን ገልፀዋል።
ዛሬ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ባለፉት ዓመታት ከተሳካው ቁጥር በላይ ሪከርዳችንን የምናሻሽልበት የይቻላል ውጤትንም የምናሳይበት ነው ብለዋል።
ዓለም እየተፈተነበት ላለው የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከልና በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት አገርን ለመታደግ ብሎም ወደተሻለ ሁኔታ ለማምጣት ኢትዮጵያ መነሳቷን ጠቁመዋል።
በዚህ ታሪካዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተሳተፉ አካላትንም አመስግነው፤ ኢትዮጵያን ጠንካራና ለዓለም ተምሳሌት ለማድረግ ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ በዛሬው እለት የሚተከሉት ችግኞች የአገሪቱን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡ ናቸው።
ይህም ብቻ ሳይሆን በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ከሚደርሰው ጉዳት ለመታደግ መርሃ-ግብሩ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራውን እንዲያኖር ጠይቀዋል።