ቀጥታ፡

ለምንተክላቸው ችግኞች ተገቢውን እንክብካቤ እናደርጋለን -የወላይታ ዞን ነዋሪዎች

ሶዶ ሀምሌ 10/2015(ኢዜአ)፡-ዛሬ የምንተክላቸው ችግኞች አረንጓዴዋን ኢትዮጵያ ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ የሚያስችሉ  በመሆናቸው ተገቢውን እንክብካቤ እናደርግላቸዋልን ሲሉ የወላይታ ዞን  ነዋሪዎች ገለጹ።

በሀገራዊ የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርኃ-ግብር ላይ በመሳተፍ ታሪክ ለመስራት ዝናብ ያልበገራቸው የዞኑ ነዋሪዎች ወደ ተዘጋጁ የችግኝ መትከያ ስፍራዎች ማልደው በመገኘት አሻራቸውን እያኖሩ ነው።

በመርኃ ግብሩ የተሳተፉት ነዋሪዎች የምንተክላቸው ችግኞች አረንጓዴዋን ኢትዮጵያ ለትውልድ ለማስተላልፍ በመሆኑ ተገቢውን እንክብካቤ እናደርግላቸዋለን ሲሉ ገልጸዋል።

ከቤተሰቦቻቸው ጋር ችግኝ የተከሉት ታዳጊ ህሊና ተስፋዬና እና ህጻን አቤኔዘር ተስፋዬ እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ ልማት የሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አሻራቸውን ማኖራቸውን ተናግረዋል።

የምንተክለው ችግኝ የተራቆቱ አካባቢዎችን አረንጓዴ በማልበስ ንጹህ አየር እንድንተነፍስ የሚያስችሉና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው ብላለች ታዳጊ ህሊና።

ህጻን አቤኔዘር በበኩሉ በልጅነት እድሜው የተከለው ችግኝ በጉርምስናው የሚጠቅመውና የተስተካከለ የአየር ንብረት እንዲኖር የሚያደርግ በመሆኑ አሻራውን ማኖሩን ተናግሯል።

የ68 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋው አቶ ግርማ ብርሃኑ በበኩላቸው ሀገር በሚያስፈልጋት ልማት ላይ ለመሳተፍ እንደማይደክሙ ገልጸዋል።

ማልደው በተገኙበት የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላም ዶማቸውን ከምድር ጋር አገናኝተው ቀኑን ችግኝ ሲተክሉ እንደሚውሉ ተናግረዋል።

"ከዚህ ቀደም በአካባቢያችን የተተከሉ ችግኞች የጠፉ የዱር እንስሳት መቦረቂያና ለእኛም ማረፊያ ሆነዋል" ብለዋል።

በችግኝ ተከላው መርሃ ግብር እስካሁን 15 ችግኞችን መትከሉን የገለጸው ወጣት አድማሱ አርባ እንዳለው ችግኝ መትከል ህይወት እንደመዝራት ነው፤ የአካባቢውን ስነምህዳር በመጠበቅ  የአፈር ለምነትን መጠበቅ ነው ብሏል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም