ቀጥታ፡

የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር አገራችን ዛሬም ታሪክ ሰሪነቷን ያስቀጠለችበት ነው-አቶ አደም ፋራህ

ባህር ዳር ሐምሌ 10/2015(ኢዜአ)፡-"መላው ህዝብ በነቂስ ወጥቶ እየተሳተፈበት ያለው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር አገራችን ዛሬም ታሪክ ሰሪነቷን ያስቀጠለችበት ነው'' ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

"ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ከተማ ዘንዘልማ ቀበሌ የአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የሀገር ጠባሳ ሆኖ የቆየውን የድርቅና የረሃብ ታሪክ ለማስቀረት የሚያስችል ነው።

ባለፉት ዓመታት በመርሃ ግብሩ በተከናወኑ ሥራዎች የተመዘገበው ውጤት አሁን ላይ በየአካባቢው ያለው ስነ-ምህዳር እንዲቀየር  ማድረጉን ገልጸዋል።

የዝናብ ስርጭት እየተስተካከለ በመምጣቱ የህዝቡ ዘላቂ ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መጥቷል ያሉት አቶ አደም፣ ህዝቡ በነቂስ የተሳተፈበት የዛሬው መርሀ-ግብርም ሀገር ታሪክ ሰሪነቷን ያስቀጠለችበት መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አቶ አደም ገለጻ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ህዝቡ ስለአረንጓዴ ልማት ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

"ከዚህ በተጨማሪ በአረንጓዴ አሻራ የሚተከሉ ችግኞች አገራችንን ለቱሪዝም፣ ለኢንቨስትመንትና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የተመቸች በማድረግ ገጽታል ለመገንባት ያስችላሉ" ብለዋል።

በመሆኑም ህዝቡ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትን በመኮትኮት፣ በመጠበቅና በመንከባከብ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ እንዳለበት አቶ አደም አሳስበዋል።

የአማራ ከልል ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው በአንድ ጀምበር ለመትከል የታቀደውን ግብ ለማሳካት መላው የክልሉ ህዝቡ ከጧት ጀምሮ እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ ነው።

"ዛሬ ችግኝ መትከላችን የነገውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት በትክክለኛው መሰረት ላይ መጣል ነው" ያሉት ዶክተር ይልቃል፣ የህዝቡ ተሳትፎ ከታቀደው በላይ ማከናወን እንደሚቻል አመላካች ነው ብለዋል።

"የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የጣና ሐይቅ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንዲሁም ሌሎች ወንዞችና ሐይቆችን ከደለል በመከላከል ለብዙ ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል በመሆኑ በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል" ሲሉም አስገንዝበዋል።

መርሀ ግብሩን በከተማና በገጠር ለጥላ፣ ለውበት፣ ለመኖና ለምግብነት የሚያገለግሉ ችግኞችን በመትከል የህብረተሰቡን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ መልኩ ማከናወን እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ናቸው።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በለሙ አካባቢዎች በጎርፍና በነፋስ ተጠርጎ ይወሰድ የነበረውን አፈር ከማስቀረት ባለፈ ለእንስሳት መኖና ለሰብል ምርታማነት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።
 

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው የፌደራል ከፍተኛ አመራር አካላት በአማራ ክልል የሚካሄደውን የክረምት ስራዎችና የሰላም ማስፈን እንቅስቃሴ ሲደግፍ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በዚህም የክልሉ ህዝብ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የዛሬውን የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላን ለማሳካት ችግኝ በማጓጓዝ፣ መትከያ ጉድጓዶችን በመቆፈርና በመትከል ያሳየው ተነሳሽነት ከዕቅድ በላይ ማከናወን እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በተለይም የክልሉ ግብርና ቢሮ እያንዳንዱ የችግኝ መትከያ ቦታን በዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓት ለመደገፍ ያከናወነው ተግባር ለሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ተሞክሮ ስለሚሆን ምስጋና ይገባዋል" ብለዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው "የአረንጓዴ ልማት ስራው በክልሉ አሲዳማ አፈር እንዲቀንስ፣ የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጨምርና የተስተካከል ዝናብ እንዲኖር እያስቻለ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም