ቀጥታ፡

በችግኝ ተከላው በአየር ንብረት ለውጥ ለሚፈተን ዓለም ባለውለታነታችንን እናሳያለን- የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ

ሚዛን አማን ሀምሌ 10/2015 (ኢዜአ) ''የችግኝ ተከላ መርሃ ግብራችንን በማጠናከር በአየር ንብረት ለውጥ ለሚፈተነው ዓለም ባለውለታነታችንን እናሳያለን'' ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ ተናገሩ።

አቶ ፀጋዬ በቤንች ሸኮ ዞን በሰሜን ቤንች ወረዳ ቦሰቃ ቀበሌ "ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ባለው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

እንደ አገር ዛሬ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል የተያዘው ሀገራዊ መርሃ ግብር በክልሉ በሁሉም መዋቅሮች እየተገበረ  ነው።


 

አቶ ፀጋዬ ባስተላለፉት መልዕክት ችግኝ መትከል የአየር ንብረት ለውጥን መቆጣጠር የአፈር ለምነት መጠበቅና ማሳደግ፣ ተፈጥሮን ወደ ነበረበት መመለስ ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር የምግብ ዋስትና በማረጋገጥና በሽታን በመቆጣጠር ድህነትን የመከላከያ መንገድ መሆኑንም አስረድተዋል።

በዚህ ሂደትም ኢትዮጵያ ለዓለም ህዝብ ምሳሌ የሚሆን ተግባር እየፈጸመች እንደምትገኝ ዋና ተጠሪው ገልጸዋል።

አያይዘውም ''የችግኝ ተከላ መርሃ ግብራችንን በማጠናከር በአየር ንብረት ለውጥ እየተፈተነ ለሚገኘው ዓለም ባለውለታነታችንን እናሳያለን'' ብለዋል።

 በአንድ ቀን ይህን ያክል ችግኝ ተክለን በዓለም የአየር ንብረት ለመለወጥ ንጹህ  አየር  በማበርከት አዲስ ስም እንይዛለን ሲሉም ተናግረዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ የዞኑ ህዝብ ህጻን አዋቂ ሳይል ለኢትዮጵያ ጉዳይ በጋራ ወጥቶ ቃልን በተግባር ለማረጋገጥ በችግኝ ተከላው እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግኝ መትከልን ማጠናከር አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴን የማስተካከል አቅም ማጠናከር ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ለዚህም ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞችን ትሩፋቶች እያየን ነው ያሉት ምክትል ዋና አስተዳዳሪው፣ ድህነትን ለማሸነፍ የጀመርነው ትክክለኛው መንገድ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የዞኑ አስተዳደርና ህብረተሰቡ በተቀናጀ መንገድ  በቀጣይ  የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ፣ በመጠበቅ  ፀድቀው ለውጤት እንዲበቁ  እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በዚሁ ቦሰቃ ቀበሌ "ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ባለው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ታዳጊ ሕፃናት፣ወጣቶች የሚያጠቡ እናቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም