እየተተከሉ ያሉ ችግኞች በቴክኖሎጂና በመረጃ የተደገፉ ናቸው - ዶክተር አደፍርስ ወርቁ - ኢዜአ አማርኛ
እየተተከሉ ያሉ ችግኞች በቴክኖሎጂና በመረጃ የተደገፉ ናቸው - ዶክተር አደፍርስ ወርቁ
አዲስ አበባ ሐምሌ 10/ 2015 (ኢዜአ) እየተተከሉ ያሉ ችግኞች በቴክኖሎጂና በመረጃ የተደገፉ መሆናቸውን የአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ ተናገሩ።
የቴክኒክ ኮሚቴው አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ በሰጡት መግለጫ በዛሬው በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ34 ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንደሚሳተፍ ገልጸዋል።
የዘንድሮ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ለየት የሚያደርገው በሚታወቅና በተለዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
ችግኞች የሚተከሉበት ስፍራና የሚተከሉበት የችግኝ ዝርያዎች ዓይነት እና ብዛት በመረጃ ተይዟል ብለዋል።
ይህም በሳተላይት ቴክኖሎጂ የተቆፈረውን ጉድጓድ ማየት የሚያስችል እንዲሁም በእነዚህ በተለዩ የችግኝ መትከያ ጣቢያዎች የመረጃ አሰጣጥ ስርዓቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የተተከሉ ችግኞች በብዙ የመረጃ ማጣራት ሂደት ውስጥ አልፈው ቁጥሮቹ ይፋ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ መሰረት እየተተከሉ ያሉ ችግኞች በቴክኖሎጂና መረጃ የተደገፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ዜጎችን በተጨባጭ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረገ መምጣቱን ገልጸው ኢትዮጵያ አረጓዴ የምትለብስበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአረንጓዴ ልማት የሰጠችውን ትኩረት በድጋሚ የምታሳይበት ነው ብለዋል።