ቀጥታ፡

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተካሄደ ይገኛል


አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2015(ኢዜአ)፦በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ለተያዘው ዕቅድ አካል የሆነ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዙሪያ እየተካሄደ ነው።

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ እንደገለፁት በመርሃ-ግብሩ ላይ በፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ እየተሳተፉ የሚገኙ ሠራተኞች እንዲሁም በፕሮጀክቱ የደህንነት ጥበቃ ላይ የተሰማሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።


 

በፕሮጀክቱ ዙሪያ የሚካሄደው የችግኝ ተከላ ሥራ ግድቡን ከደለል በመከላከል ኃይል የሚያመነጭበትን እድሜ ለማራዘም እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የችግኝ ተከላ ሥራው የሀገሪቱን የዝናብ ሁኔታ ሚዛናዊ ለማድረግና የደን ሽፋኑን ቀድሞ ወደ ነበረበት ለመመለስ ዕድሉ የሰፋ እንደሆነም ገልጸዋል።

ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚከናወንበት አካባቢ በደን የተሸፈነ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ የችግኝ ተከላ ሥራው በአካባቢው ያለውን የአረንጓዴ ልማት አስጠብቆ ለማቆየት ፋይዳው የጎላ እንደሆነም አመላክተዋል።

በፕሮጀክቱ ዙሪያ ከዚህ በፊት የችግኝ ተከላ ሥራ ሲከናወን እንደነበር አስታውሰው በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የግድቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ህብረተሰቡ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ኢንጅነር ክፍሌ ጥሪ አቅርበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት በፕሮጀክቱ ላይ ሠራተኛ የሆኑት አቶ ያሬድ ግርማ በበኩላቸው አለም ዐይኑን ገልጦ በሚመለከተው ሀገራዊ ፕሮጀክት የግንባታ ሥራ ላይ ከመሳተፋቸው ጎን ለጎን በሀገራዊ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ላይ መሳተፋቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።

የተከላ ሥራው በግድቡ ዙሪያ መከናወኑ በተፋሰሱ ላይ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልና የዝናብ መጠንን ለመጨመር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

የዊ ቢውልድ/ሳሊኒ/ ኩባንያ ሠራተኞች ማህበር ተወካይ አቶ ሞገስ የሺዋስ በበኩላቸው በችግኝ ተከላ ሥራው ላይ የኩባንያው ሠራተኞች እየተሳተፉ እንደሚገኙ በመግለፅ በቀጣይ ከፕሮጀክት ቢሮው ጋር በመተባበር ሠራተኞች በችግኝ ተከላ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል።

በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉት በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ20ኛ ክፍለ ጦር አባል መቶ አለቃ ድረስ ያለውና የፌዴራል ፖሊስ አባል ኮማንደር ጀማል አደም የፕሮጀክቱን ደህንነት ለማስጠበቅ እየሠሩት ካለው የሠላም ማስከበር ሥራ በተጨማሪ "ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል ሀገራዊ ጥሪ እየተከናወነ ባለው የችግኝ ተከላ ሥራ ላይ መሳተፋቸው ትልቅ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ በቀጣይ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።

በዕለቱ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች እየተተከሉ ሲሆን ይህም በምግብ ራስን ለመቻል እየተሰራ ያለውን ሥራ በመደገፍ በኩል የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም