የአረንጓዴ አሻራ ልማት በድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ በመቀነስ የህብረተሰቡን ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል- ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ ልማት በድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ በመቀነስ የህብረተሰቡን ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል- ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ
ድሬዳዋ ሐምሌ 10/2015(ኢዜአ) ፡- የአረንጓዴው አሻራ ልማት በድሬዳዋ ይከሰት የነበረውን የጎርፍ አደጋ በመቀነስ የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ተናገሩ።
የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ፤በድሬዳዋ በይፋ በተጀመረበት ወቅት ምክትል ከንቲባው፤ ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተከናወኑ ስራዎች በድሬዳዋ ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህም በድሬዳዋ ይከሰት የነበረውን የጎርፍ አደጋ በመቀነስ የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና እንዲያረጋግጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ የኢትዮጵያን ከፍታ ማረጋገጫ ወሳኝ ጉዳይ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ የኢትዮጵያ ስምና ዝና ከፍ የሚያደርግ ይሆናል ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ መትከልና መንከባከብ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አስረድተዋል።
ዛሬ እንደ ሀገር እየተካሄደ የሚገኘውን የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አካል የሆነውን የድሬደዋ መርሃግብር ለማሳካት መላው የአስተዳደሩ ነዋሪዎች እያደረጉ ላሉት ርብርብ አመሰግነዋል።
በአስተዳደሩ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ላይ ከሚገኙት የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱአለም በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ የተተከሉት ችግኞች ለምለሟና አረንጓዴዋን ኢትዮጵያን የመገንባት ስራ በስኬት እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።
ይህንኑ አበረታች ውጤቶች ይበልጥ በማጠናከር የደን ሃብትን ብሎም ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትጋትና በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሚተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ማሳደግ ላይ ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ መልዕክት አስተላልፈዋል ።
በመረሃ ግብሩ ላይ የፕላንና የልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ ዲያስፖራው ማህበረሰብ ፤ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።