ቀጥታ፡

የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከማለዳው ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ መከናወኑን ቀጥሏል

አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2015(ኢዜአ) የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከማለዳው ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ መከናወኑን ቀጥሏል።

ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮችና አባላት፣ ታዳጊዎች፣ አረጋዊያን፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎችም የማኅበረሰብ ክፍሎች እየተሳተፉበት ያለው የአንድ ጀምበር የ500 ሚሊዮን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከማለዳው ጀምሮ በመከናወን ላይ ይገኛል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በዛሬው እለት በየግላቸው 100 ችግኞችን ለመትከል አቅደው ከማለዳው ጀምሮ አሻራቸውን በማኖር ላይ ናቸው።

በአዲስ አበባ፣ በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮችም የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ "ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናልብስ፤ ነገን እንትከል፤ ታሪክን እንትከል" በሚል መርህ የአንድ ጀምበር የ500 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል።


 

በዚሁ መርሃ-ግብር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ፣ በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 አሻራቸውን አኑረዋል።


 

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከአገር የሚሻገር ዓላማን ሰንቆ ለአህጉራዊ ብሎም ዓለም አቀፍ ጠቀሜታ ፋይዳ ያለው መሆኑን ምክትል አፈ-ጉባዔዋ ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ በበኩላቸው፤ ዓለምን በእጅጉ እየፈተነ ያለውን የአየር  ንብረት ለውጥ ለመከላከልና ለመቋቋም ችግኞችን መትከል የላቀ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያ በልዩ ትኩረት እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።


 

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታትም ከ25 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ካሳካችው ዕቅድ በመነሳት የሁለተኛውን  ምዕራፍ  አገር  አቀፍ  ንቅናቄ  ቀጥላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም