የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አመራሮች እና ሰራተኞች አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አመራሮች እና ሰራተኞች አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ
አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2015 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አመራሮች እና ሰራተኞች በጉለሌ እጽዋት ማዕከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ልማት በአንድ ጀምበር የ500 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሐ-ግብር ዛሬ ማለዳ መካሄድ ጀምሯል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች በመርሐ-ግብሩ ላይ በመሳተፍ አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አመራሮች እና ሰራተኞችም የዚሁ አካል የሆነውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር አከናውነዋል።
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል የአረንጓዴ አሻራ የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ ወሳኝ ስራ መሆኑን ገልጸው ካለው የኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አኳያ ስራው በተጠናከረ መልኩ ማከናወን እንደሚገባ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ተፈራ በቀለ በበኩላቸው ሕብረተሰቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግኝ የመትከል ባህሉ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ችግኝ መትከል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው ተግባራቱን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።