ጥንዶቹ የጋብቻ ስነ ስርዓታቸውን ችግኝ በመትከል አከበሩ - ኢዜአ አማርኛ
ጥንዶቹ የጋብቻ ስነ ስርዓታቸውን ችግኝ በመትከል አከበሩ
ሆሳዕና ሐምሌ 9 /2015 (ኢዜአ) በሀድያ ዞን ሾኔ ከተማ ጥንዶች የጋብቻ ስነ ስርዓታቸውን ችግኝ በመትከል አከበሩ።
ጥንዶቹ የችግኝ ተከላዉን ያካሄዱት " ነገን ዛሬ እንትከል " የሚለውን መርህ በመከተል ነው።
በሾኔ ከተማ ሊቻ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ረታ ወልቃ ለኢዜአ እንደገለጹት ችግኝ መትከል የሰው ልጆችን የህይወት እንቅስቃሴ ጤናማ የሚያደርግ ወሳኝ ተግባር ነው።
በችግኝ ተከላ ላይ የሚደረግ ርብርብ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው፤ ያሉት ሙሽራው ይህን በመረዳት ሰርጋቸውን ችግኝ በመትከል ማክበራቸውን አመክተዋል።
"በዚህም ከፍተኛ የሆነ ኩራትና ደስታ ይሰማኛል" ብለዋል።
ነገ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንዲሳካ ያላቸውን ምኞች ለማሳየት ዛሬ የሰርጋቸውን ስነ ስርዓት 200 ችግኞች በመትከል መክበራቸውን ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትግበራ የሀገሪቱን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማሳደግ በተጨማሪ ሁለንተናዊ ጉዞዋን ለማሳለጥ የሚያግዝ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በተግባሩ በመሳተፍ መረባረብ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ሙሽሪት ፍሬህይወት ብርሃኑ በበኩላቸው የሀገርን ልዕልና አስጠብቆ ለማስቀጠል ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።
"አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትግበራ የሀገራችንን ከፍታ ለማረጋገጥ አስተዋጾው ከፍተኛ ነው በመሆኑ "ተግባሩ ለማጠናከር ዕለቱን ችግኝ በመትከል ለማሳለፍ ተጠቅመናል " ብለዋል ።
የሰርግ ስነ ስርዓታቸውን ከሚዜዎቻቸው፣ አጃቢዎቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ችግኝ በመትከል ለማሳለፍ ከባለቤታቸው ጋር መግባባት ላይ በመድረሳቸው ጋብቻቸውን ችግኝ በመትከል ማክበራቸውን አስታውቀዋል።
የተከሉትን ችግኝ በመንከባከብ ለታቀደው ዓላማ እንዲውል የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡም አመላክተዋል ።
በብልፅግና ፓርቲ የሾኔ ከተማ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበራ በዶሬ ጥንዶቹ በሾኔ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ጊቢ ችግኝ በመትከል የሰርግ ስነ ስርዓታቸውን ማክበራቸውን ጠቁመው "ይህም አርአያ ያደርጋቸዋል "ብለዋል
"ጥንዶቹ 200 ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መትከላቸው ነገን የተሻለ ህይወት ለመኖር የሚያስችል አስተዋፖ ያበረክታል" ብለዋል"
በነገው ዕለት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በሾኔ ከተማም ከ100 ሺህ በላይ የተለያየ ዝርያ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።