ቀጥታ፡

ዛሬ የምንተክለው ችግኝ የነገ ምግባችን፣ መጠለያ ጥላችን እንዲሁም የአየር ብክለት መከላከያ ጋሻችን ነው--ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ሐምሌ 9/2015(ኢዜአ)፦ ዛሬ የምንተክለው ችግኝ የነገ ምግባችን፣ መጠለያ ጥላችን እንዲሁም የአየር ብክለት መከላከያ ጋሻችን ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ነገ የሚከናወነውን በአንድ ጀምበር የ500 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሃ-ግብር በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም “በነገው ዕለት የአዲስ አበባ ነዋሪ ተምሞ 'ነገን ዛሬ ለመትከል' ይወጣል፤ አዲስ አበባ ታሪክ ለመትከል ተዘጋጅታለች" ሲሉ ገልጸዋል።

ዘመናትን የተሻገረ የሃገር ፍቅር ባለቤት የሆው መላው የከተማችን ነዋሪ ኢትዮጵያ ከምትተክለዉ ከ500 ሚሊዮኑ ችግኞች ውስጥ አዲስ አበባ ከ4 ሚሊዮን በላይ በመትከል ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ አሻራችንን በማስቀመጥ የዚህ አኩሪ ታሪክ አካል እንሆለንም ብለዋል ከንቲባዋ።

ዛሬ የምንተክለው ችግኝ የነገ ምግባችን፣ መጠለያ ጥላችን እንዲሁም የአየር ብክለት መከላከያ ጋሻችን ነው ሲሉም ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከንቲባ አዳነች አክለውም በዚህ ታሪካዊ ቀን የመንግስትና የግል ሰራተኞች፣ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ሰራተኞች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ መምህራን፣ ነጋዴዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ተማሪዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ ሴቶች፣ የከተማችን ወጣቶች፣ ባለሃብቶች፣ አርቲስቶች፣ የስፖርት ቤተሰቦች፣ የሚዲያ ባለሞያዎች፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች እንዲሁም በልዩ ልዩ ሙያ ላይ የተሰማራችሁ የከተማችን ነዋሪዎች ነገ ተምመን ለመላው ዓለም የተባበረ ክንዳችንን እና ስንተባበር ምን መስራት እንደምንችል የምናሳይበት ታሪካዊ እለት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም መዲናችን የኢትዮጵያ ማሳያ መልክ እንደ መሆኗ ነገ ይህን በተግባር የምታሳይበት ዕለት ስለሆነ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምራችሁ በከንቲባ ጽህፈት ቤት ወይም Mayor Office የፌስቡክ ገፅ እና በአዲስ ሚዲያ የቀጥታ ዘገባ የሚተላለፍ ሲሆን በየአካባቢያችሁ በተዘረዘሩ የመትከያ ቦታዎች በመገኘት በዚህ ታሪካዊ እለት አሻራችሁን እንድታኖሩ በአክብሮት ጥሪየን አቀርባለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም