ቀጥታ፡

የትምህርትና የሀይማኖት ተቋማት ለተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ሊያጠናክሩ ይገባል--ቢሮው

ቦንጋ ሐምሌ 9/2015(ኢዜአ) የትምህርትና የሀይማኖት ተቋማት ለተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አካባቢ ጥበቃ፣ ደን ልማትና አየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ቢሮ ጠየቀ።

የኢትዮጵያ ሥነ-መለኮት ድህረ-ምረቃ ኮሌጅ ከቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ጋር በመተባበር "ትምህርት ለዘላቂ ልማት" በሚል መርህ ያዘጋጁት ዓመታዊ ጉባኤውን አካሂዷል።

በጉባኤው ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አካባቢ ጥበቃ፣ ደን ልማትና አየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አስራት ገብረማርያም የትምህርትና የሀይማኖት ተቋማት ለአካባቢ ጥበቃ የማይተካ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

ተቋማቱ ይህን ወሳኝ ሥራ በቀጣይም አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ወቅቱ ለአካባቢና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ትልቅ ትኩረት ከመስጠት ባለፈ በስፋት ግንዛቤ መፍጠር የሚያስፈልግበት መሆኑንም ዶክተር አስራት አንስተዋል።

"በዚህ በኩል የሀይማኖት እና የትምህርት ተቋማት ህብረተሰቡን በማንቃትና ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርግ በማድረግ በኩል ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል" ብለዋል።

አካባቢን ጠብቆና አልምቶ ለኑሮ ምቹ በማድረግ ለትውልድ የማስተላለፍ ጉዳይ ለአንድ ወገን የሚተው እንዳልሆነ በመረዳት መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የቱሪስት መስህብ የሚሆኑ ቦታዎች ያሉት፤ በተፈጥሮ ሀብቱም በተለይ የብዘሃ ሀብት ክምችት ያለበት በመሆኑ እነዚህን ሀብቶች ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ መሆኑንም ዶክተር አስራት አንስተዋል።
 

ጉባኤው "ትምህርት ለዘላቂ ሰላም" በሚል መርህ ሀሳብ ቢካሄድም ዋና አላማው አካባቢ ጥበቃ ላይ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ዲን አቶ አንተነህ አየለ ናቸው።

ዲኑ እንደገለጹት የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ለተማሪዎች ከሚሰጠው የንድፈ ሀሳብ ትምህርት በተጨማሪ አካባቢ ጥበቃ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው።

አካባቢን መጠበቅ ትውልድን ከማስቀጠልና ከዘላቂ ልማት ጋር በቀጥታ እንደሚገናኝም አቶ አንተነህ አንስተዋል።

በተለይም  እንደሀገር  አካባቢን ለመጠበቅና ለማልማት እየተደረገ ባለው ርብርብ የትምህርት እና የእምነት ተቋማት በሰፊው ሊሳተፉ እንደሚገባ ገልጸው፣ በእዚህ በኩል የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
 

ለተፈጥሮ ሀብት ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ለቀጣይ ትውልድ ያልተጎሳቆለ አካባቢ ለማቆየት አበክሮ መስራት ይግባል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የስነ-መለኮት ድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ተወካይ ዲን ዶክተር ልደቱ አለሙ ናቸው።

በእዚህ ረገድ ከፍተኛ የትምህርትና የእምነት ተቋማት ስራዎችን በጥናትና ምርምር አስደግፎ ለችግሮች መፍትሔ የማበጀት ትልቅ ሀላፊነት እንዳለባቸው አንስተዋል።

"አካባቢን ሳንጠብቅና ሳንንከባከብ ቀጣይነት ያለው ልማት ማምጣት የማይታሰብ ጉዳይ ነው" ያሉት ዶክተር ልደቱ፤ ለውጥ ለማምጣት ተባብሮና ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። 

ስምንት የመንግስትና ትምህርትና አራት የስነ-መለኮት ኮሌጆችን በአባልነት የያዘው ጥምረቱ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን የሚያጠናክሩ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነም ዶክተር ልደቱ ገልጸዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኘውን የተፈጥሮ ድልድይ፣ የውሽውሽ ሻይ ልማት እንዲሁም በዩኔስኮ የተመዘገበውን የቆምባ ዳጋ ጥቅጥቅ ደንን ጎብኝተዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም