ቀጥታ፡

ችግሮችን በውይይትና በስርአተ ቤተክርስቲያን በመፍታት እየተስተዋለ የመጣውን ራስን በራስ የመሾም አባዜ መግታት ይገባል - ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

አዲስ አበባ ሐምሌ 9/2015(ኢዜአ)፦ "ማንኛውንም ችግር በውይይትና በምክክር በመፍታት የተበደለውን በመካስ በቤተ ክርስቲያኗ የሚስተዋልን ራስን በራስ የመሾም አባዜ መገታት አለበት" ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አሳሰቡ።

ቤተ ክርስቲያኗ ለዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት በዓለ ሢመት በመፈጸም ለአህጉረ ስብከቶቿ የስራ ኃላፊነት ምደባ ሰጥታለች።

ሥርዓተ ሲመትና የስራ ኃላፊነቱም የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ መሠረት ለዘጠኙ ቆሞሳት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መሪነት በሊቃነ ጳጳሳት አንብሮተ ዕድ ተፈጽሟል፡፡

በዚሁ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፦ ጸጋዎቹ ለሰው ልጆች እኩል አስፈላጊ እንደሆኑ አውቆ መንፈስ ቅዱስ ለሰው ይሰጣል ሰዎች ግን አንዱ ትንሽ ሌላው ትልቅ ጸጋ እንደሆነ አድርገው በመውሰድ ግራ ይጋባሉ ብለዋል።

ይህን ዓይነቱን አመለካከት በቤተ ክርስቲያን ቦታ እንዳያገኝ በጽናት መቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሐዋርያዊ ቀኖና እና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተመረጡ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመትም በጸጋ መንፈስ ቅዱስ መሠረት እንደሆነ ገልጸዋል።

ሹመት የተሰጣቸው ኤጲስ ቆጶሳትም የሚሊዮኖች ዓይኖች እነሱን ይመለከታሉ፤ ትምህርቱን፣ ንጽህናውን ቅድስናውን፣ ትጋቱን፣ ሃይማኖቱን፣ ጸሎቱን፣ ፍቅሩን፣ አመራሩን፤ አኗኗሩን፤ አነጋገሩን፣ በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ሕይወቱ ለምእመናን ዓይንና አእምሮ የተጋለጠ መሆኑን ተገንዝቦ ለብዙዎች የመዳን መሪና ፊታአውራሪ ሆነው ማገልገል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ባልተጠበቀና ባልተለመደ ሁኔታ ብቅ ብቅ ሲሉ የሚታዩት ራስን በራስ የመሾም አባዜ መገታት አለባቸው ያሉት አባ ማትያስ ማንኛውም ችግር በውይይት፣ በምክክርና የተበደለውንም በመካስ መፈታት ይገባዋል ብለዋል።

በጥፋት ላይ ጥፋት እየተከሠተ የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚፈታተን ድርጊት በማቆም ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዲከብርና እንዲጠበቅ በትጋት መስራት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።

በቤተክርስቲያኗ ሥርዓተ ሢመት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት እና ምክትል ፕሬዚደንቷ ወይዘሮ አበባ እምቢአለ፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍንን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች እና የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም