ቀጥታ፡

ነገን ዛሬ ለማጽናት - አረንጓዴ አሻራ

(ብርሃኑ አለማየሁ)

ከሰው ልጅ ዋነኛ ተግባራት አንዱ ተፈጥሮን መጠበቅና መንከባከብ ነው። ተፈጥሮን ሲጠብቃትና ሲንከባከባት ደግሞ አብልጣ ትክሰዋለች። ምድር ሙሽራ ትሆናለኝ። መልካምን ፍሬ አብዝታ ታፈራለች። ንጹህ አየር ከባቢውን ይቆጣጠራል። ተስፋውን ታጸናለች።  የሰው ልጅ እርሱነቱ ይታደሳል። ይህ የሰው ልጅ ላለፉት ረጅም ዓመታት በተፈጥሮ ላይ ያደረሰው ጉዳትና እርሱን ተከትሎ የመጣውን ጥፋት በጥልቀት ከተመረመረ በኋላ በተገኘው ሀሳብ ላይ ተመርኩዞ የተሰነዘረ ነው። የሰው ልጅ ያጠፋትን ተፈጥሮ መንከባከብ መልሳ እንደምትክሰው ያሳያል። እውነት የሰው ልጅ ተፈጥሮን እንዴት ጎዳት? የሚል ጥያቄ ብናነሳ የምናገኘው ምላሽ ያስደምማል። እያንዳንዱ ሰው የየራሱ መልስ አለው። አካባቢው በማራቆት፣ ደን በመጨፍጨፍ፣ ለከባቢ አየር አመቺ ያልሆኑ በካይ ጋዞችን በመልቀቅ ጥፋቱ ከዕለት ዕለት እየሰፋ መምጣቱ የአደባባይ ምስጢር ነው። በተለይ የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ተብሎ የተዘጋጁ ኬሚካሎች የጎንዮሽ ችግሮችን መፍጠርና የተፈጥሮን ከባቢ አየር የሚበክሉ ኬሚካሎች ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመርና ሌሎች ምክንያቶች ተፈጥሮ እንድትጎዳ ሆኗል።  

ለአብነት ከኢንዱስትሪ የአብዮት ዘመን አንስቶ ባለው ዘመናዊ የኑሮ ዘይቤ ጀምሮ ያለውን ብንመረምር የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር በመጣላቱ የደረሰበት ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። እንደየአካባቢው ሁኔታ የአየር ንብረት በመቀየሩ ለከፍተኛ ቅዝቃዜና ዝናብ፣ ጎረፍና ሰደድ እሳት እንዲጋለጡ ምክንያት ሆኗል። በዚህም ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል። መሰረተ ልማቶች ፈርሰዋል። የእርሻ መሬቶች ጥቅም አልባ ሆነዋል። ምድር እንድትጎሳቆል፤ በረከቷን እንዳትሰጥ ምክንያት ሆነዋል። እኤአ በ2022 በአውሮፓ በተከሰተ ከፍተኛ ሙቀትና ቅዝቃዜ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ60 ሺህ በላይ መድረሱን በቅርቡ አንድ ሪፖርት ያወጣውን መረጃ በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል። በሰው ልጅ የማያልቅ የእድገት ፍላጎት የመጣው አደጋ በአንድ አካባቢ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ባለመሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገሮችም የችግሩ ተቋዳሽ ለመሆን ተገደዋል።

ተፈጥሮ ያለ ስስት የሰጠችውን ጻጋ የሰው ልጅ በአግባቡ አለመጠቀሙ የጋረጠበትን የህልውና አደጋ በመገንዘብ መንግስታት ተፈጥሮን ለማከምና እንድታገግም ለማድረግ የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰዱ ይገኛል።

ለዚህ ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የጸደቀውና ወደ ከባቢ የሚለቀቅ በካይ ጭስ የመቀነስ ድንጋጌን ጨምሮ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ንቅናቄ አጀንዳዎች ተጠቃሽ ተግባራት ናቸው።

አገሮች ተፈጥሮን ለማከም በተመድ የጸደቁትን አጀንዳዎች ጨምሮ እንደየአካባቢያቸው ባህሪያት ተስማሚ የሆኑ ተግባራትን በመወጠንም እየሰሩ ይገኛል። የአረንጓዴ ኢኮኖሚና ልማትን በማቀድና በመተግበር ዴንማርክ፣ አይስላንድና ኔዘርላንድ ከጎረቤት አገራችን ደግሞ ኬኒያና ኡጋንዳ ተጠቃሽ ናቸው።

ኢትዮጵያም የዚሁ አጀንዳ አካልና ለሌሎች ተሞክሮ የሆነ “የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ” መርሐ ግብር ቀርጻ ላለፉት አምስት ዓመታት በመጀመሪያና ሁለተኛ ምዕራፍ እየተገበረች ትገኛለች።

አረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥን እና የአካባቢ መራቆትን ለመቋቋም የተወጠነ አገር በቀል መርሃ ግብር ነው። ይህ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ፋይዳው በተጨማሪ ለምግብ የሚውሉ ዕጽዋትንም በመትከል የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ዓላማ ያደረገ መሆኑ ነው።

በአረንጓዴ አሻራ የመጀመሪያው ምዕራፍ 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ለአካባቢ ጥበቃ ያለትን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይታለች። ዘንድሮ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተተከሉት ችግኞች 31 ቢልዮን ይደርሳሉ።

“ነገን ዛሬ እንትከል” የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የሁለተኛው ምዕራፍ መሪ ሐሳብ ሲሆን፤ በመርሐግብሩ ለፍራፍሬ ዛፍና ለጥምር ደን ዛፎች ትልቅ ትኩረት በመስጥ ወደ ስራ መገባቱ ተመልክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ የሚካሄደውን 500 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር የመትከል መርሐ ግብር በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት “አረንጓዴ ዐሻራ” ለእኛ ብዙ ነገራችን ነው” ብለዋል።

መርሐ ግብሩ “የግብርና ምርታችንን ከፍ የሚያደርግና በምግብ ራሳችን እንድንችል የሚያበቃን፣፡ ሁለት ሦስት ጊዜ አምርተን የምግብ ምርት በርካሽ እንዲገኝ የሚያስችል እና ወንዞች እስከ ወሰናቸው እንዲሞሉ አድርጎ መስኖና የመጠጥ ውኃ እንዳይቋረጥ በማድረግ የደን ሽፋን አሳድጎ የአየር ንብረቱን የሚያስተካክል ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች የሚኖረውን ሁሉን አቀፍ ፋይዳ ባሳዩበት መልዕክታቸው  ተራሮች፣ የወንዝ ግራና ቀኞች፣ የመንገድ አካፋዮች፣ የቤቶቻችን ግቢዎች፣ የሠፈሮቻችን ባዶ ሥፍራዎች፣ የቤተ እምነቶች ቅጽረ ግቢዎች፣ የየትምህርት ቤቱ እና የየመሥሪያ ቤቱ ግቢዎች፣ ለግብርናና ለእንስሳት ግጦሽ የማይውሉ መሬቶች “በደን መሸፈን አለባቸው” በማለት ኢትዮጵያውያን እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ ተፈጥሮን በማከም ይዞ የሚመጣው ትሩፋት ዘርፈ ብዙ ነውና ለትውልድ የሚተርፍ ቅርስን ለመስራት ነገን ዛሬ እንትከል።

ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ/ም ጀንበር ወጥታ እስክትገባ ማንኛውም “ኢትዮጵያዊ ቤቱ አይውልም ከጀንበር በኋላ እንመለሳን ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናለብሳለን” የነገን ህልም ዛሬ ለማጽናት የሚተገበር መርሃ ግብር። አይቀርም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም