ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩን ለማሳካት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ስለመኖሩ መታዘቡን የፌዴራል መንግስት የድጋፍና ክትትል ቡድን ገለጸ

ባምቤላ ሐምሌ 9/2015(ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማሳካት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እንደተከናወነ የፌዴራሉ የድጋፍና የክትትል ቡድን መታዘቡን ገለፀ።

የፌዴራሉ የድጋፍና የክትትል ቡድን አባላት ከክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን በአይነቱ ልዩ የሆነዉን የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን ተዘዋውረዉ ጎብኝተዋል።

ከቡድኑ አባላት መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ዳባ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ባደረጉት ምልከታ በአንድ ጀምበር የሚካሄደውን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለማሳካት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ስለመከናወናቸው በመስክ ምልከታ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ያሉት ዞኖችና ወረዳዎች ያደረጉት ዝግጅት በክልሉ በአንድ ጀምበር ሊተከል የታቀደውን ግብ ማሳካት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

እንደ ፌዴራል ድጋፍና ክትትል ቡድንም ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በዕለቱ የተያዘው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ስኬታማ እንዲሆን የድጋፍና የክትትል ስራቸውን እንደሚያጠናክሩ አብራርተዋል።

በክልሉ ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተደረገው ዝግጅት አመርቂ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት ምክትልዋና ዳይሬክተር አቶ አለሙ አኖ ናቸዉ ።

በዕለቱ በክልሉ ለመትከል የታቀደውን ግብ ለማሳካት የቡድኑን አባላትን ጨምሮ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ላክዴር ላክባክ በበኩላቸው ከፌዴራል የድጋፍን የክትትል ቡድን ጋር በመሆን የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ያለውን ዝግጅት ተዘዋውረው መመልከታቸውንና ሂደቱም አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የድጋፍና የክትትል ቡድኑ በክልሉ በፈጠረው ንቅናቄ በሁሉም አካባቢዎች በቂ ዝግጅት በማድረግ ህዝቡም ሆነ አመራሩ ዕለቱን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ-ግብር የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በመጨመር ዘላቂ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የማጃንግ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ማይክል ናቸዉ።

የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የፌዴራል የድጋፍና የክትትል ቡድኑ በዛሬው ዕለትም በማጃንግ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን ዛሬም ጉብኝቱ በጋምቤላ ከተማ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም