የአረንጓዴ አሻራ ልማት የቀጣዩ ትውልድ ዋስትና እና የአገር የእድገት መሰረት በመሆኑ ለስኬቱ የሁሉም ተሳትፎ ሊታከልበት ይገባል-ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ ልማት የቀጣዩ ትውልድ ዋስትና እና የአገር የእድገት መሰረት በመሆኑ ለስኬቱ የሁሉም ተሳትፎ ሊታከልበት ይገባል-ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና
አዲስ አበባ ሐምሌ 9/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የቀጣዩ ትውልድ ዋስትና እና የአገር የእድገት መሰረት በመሆኑ ለስኬቱ የሁሉም ተሳትፎና ጥረት ሊታከልበት ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ገለፁ።
በዓለም ላይ እየበረታና እየተስፋፋ የመጣው የሙቀት መጠን መጨመር የሰው ልጆችን ጨምሮ በምድር ላይ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ እየጎዳና የቀውስ ምክንያትም ሆኖ ቀጥሏል።
የዓለምን የተፈጥሮ ዑደት በማዛባት ምድር በውስብስብ ችግሮች እንድትፈተን ዋነኛ ምክንያት እየሆነ የመጣውም የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑን በርካታ የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ።
ለሰው ልጆች የጤና መቃወስና ለተለያዩ ሕመሞች መዳረግ፤ የድርቅ መፈራረቅና የጎርፍ አደጋ እንዲሁም የግብርና ምርት ለመቀነሱ የአየር ንብረት ለውጥ አንደኛው ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል።
በተለይም በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የችግሮቹ ገፈት ቀማሽ በመሆን የጉዳታቸው መጠን ከዓመት ዓመት እየበረታ ይገኛል።
በመሆኑም ይህንን ዓለም አቀፍ ችግር በመከላከልና በመቋቋም በኩል ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት መርሃ-ግብር ነድፋ ተግባራዊ እንቀስቃሴዎችን ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል።
በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል በሁለተኛው ምዕራፍም የተሻሉ ውጤቶችን ለማስመዝገብ አገር አቀፍ ንቅናቄ ጀምራለች።
ሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም በአፋር ክልል በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
የሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አካል የሆነው የአንድ ጀምበር የ500 ሚሊዮን የችግኝ ተከላ በነገው እለት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወን ይሆናል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ የአረንጓዴ አሻራ ልማቱ የአገሪቱን የደን ሽፋን በማሳደግና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመቋቋም ለምጣኔ ሃብት እድገትና ልማት የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የመጪው ትውልድ ዋስትና እና የአገር የእድገት መሰረት በመሆኑ ለስኬቱ የሁሉም ጥረት ሊታከልበት ይገባል ሲሉ ተናግረዋለ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ከመማር ማስተማርና ከምርምር ሥራው ባሻገር በማህበረሰብ አገልግሎት ለአረንጓዴ አሻራ ልማት የደርሻውን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በነገው እለት በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር መሳካት በተለያየ መልኩ ለመሳተፍ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።
የችግኝ ተከላው በመንግስት ጥረትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ በጥሩ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰው ለጽድቀቱም የእንክብካቤ ባህልን ማዳበር ይገባል ብለዋል።