ቤተክርስቲያኗ ለዘጠኙ ኤጲስ ቆጶሳት በዓለ ሢመት በመፈጸም ለአህጉረ ስብከቶች የስራ ኃላፊነት ምደባ ሰጠች

አዲስ አበባ ሐምሌ 9/2015(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለዘጠኙ ኤጲስ ቆጶሳት በዓለ ሢመት በመፈጸም ለአህጉረ ስብከቶች የስራ ኃላፊነት ምደባ ሰጥታለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ መሠረት ለዘጠኙ ቆሞሳት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መሪነት በሊቃነ ጳጳሳት አንብሮተ ዕድ ተፈጽሟል፡፡

ሥርዓተ ሲመትና የስራ ምደባውም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሰረት ሐምሌ 9/2015 ዓ.ም የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ሥርዓት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተከናውኗል።

በዚሁ መሰረትም የዘጠኙ ኤጲስ ቆጶሳት ስያሜ እና የተመደቡባቸው አህጉረ ስብከት እንደሚከተለው ቀርቧል።

1. አባ ክንፈገብርኤል ተ/ማርያም ብፁዕ አቡነ ገሪማ፦ ጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

2. አባ ሣህለማርያም ቶላ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት

3. አባ ስብሐት ለአብ ኃይለማርያም ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት

4. አባ አምደሚካኤል ኃይሌ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፡- ምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት

5. አባ ኃይለማርያም ጌታቸው ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ፣ ድሬዳዋ ሀገረ ስብከት

6. አባ ጥላሁን ወርቁ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም፡- ቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት

7. አባ ዘተ/ሃይማኖት ገብሬ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ፡- ሆሮ ጉድሩ ሀገረ ስብከት

8. አባ አስጢፋኖስ ገብሬ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል፡- ምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት እና

9. አባ ወ/ገብርኤል አበበ ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ ምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሆነው ሹመትን እና የሀጉረ ስብከት የስራ ኃላፊነትን ተረክበዋል።

ሥርዓቱም ከሌሊት ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቀኖናን በጠበቀና በተከተለ መልኩ በሥርተ ቅዳሴ እና ጸሎት በድምቀት ተከናውኗል።

በሥርዓተ ሢመትና የስራ ምደባው ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ኃይማኖት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸኃፊ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር)፣ የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና የእምነቱ ተከታይ ምዕመናን በተገነኙበት ተከናውኗል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም