የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ማኅበር በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ማኅበር በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ማኅበር በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሠነድ ሥምምነት ተፈራረሙ።
ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖና የኢትዮጵያ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሳሚያ አብዱልቃድር ዛሬ ማምሻውን ፈርመውታል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ባንኩ በአገሪቱ ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎ የሚያደርግ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋም ነው።
በዛሬው ዕለትም የወጣቶችን የሥራ ፈጠራ ከሚያበረታታው ከኢትዮጵያ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት መፈራረሙን ጠቁመዋል።
ሥምምነቱ የሥራ ፈጠራ ባለቤቶች በማበረታታት በአገሪቱ ለሥራ ፈጠራ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርና በባንኩና በማኅበሩ መካከል ጠንካራ አጋርነት ለመመሥረት ያለመ ነው ብለዋል።
ሥምምነቱ የተለያዩ የሥራ ፈጠራ ባለቤት ለሆኑ ወጣቶች የፈጠራ ሃሳባቸውን ወደ ንግድ በመለወጥ ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራልም ነው ያሉት።
በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተመሰከረላቸው የፈጠራ ሥራ ባለቤቶች አስፈላጊውን ብድርና ሌሎች የባንክ አገልግሎቶች እንደሚያቀርብ ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።
ባንኩ በቀጣይም ከማኅበሩ ጋር ያለውን አጋርነት በማጠናከር በአገሪቱ አማራጭ የልማት ሞዴል ተግባራዊ እንዲደረግና የአገሪቱን እድገት ለማስቀጠል እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሳሚያ አብዱልቃድር በበኩላቸው በሁለቱ ተቋማት የተደረሰው ሥምምነት አጋርነትን ያጠናክራል ብለዋል።
በተለይም ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ያሉባቸውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በመቅረፍና ሃሳባቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጡ በማድረግ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት።