ቀጥታ፡

በሐድያ ዞን እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራት አበረታችና ተጨባጭ ውጤት የሚታይባቸው ናቸው - ኢንጂነር አይሻ መሐመድ

ሆሳዕና ሐምሌ 8/2015 (ኢዜአ) --በሐድያ ዞን እየተካሄዱ የሚገኙ የልማት እንቅስቃሴዎች አበረታችና ተጨባጭ ውጤት የሚታይባቸው  መሆናቸውን የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለጹ።

የዞኑ ህዝብ እንደ ሀገር በመጣው ለውጥ ተነሳስቶ ዕምቅ የልማት አቅሞችን ወደ ልማት በመቀየር ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው አበረታች የልማት እንቅስቃሴ ለሌሎች አከባቢዎች እንደ ምርጥ ተሞክሮ ተደርጎ እንደሚወሰድ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን በሕዝብ የተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ገለጻ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ወደ ክልሎች በመሄድ የክትትልና የድጋፍ ሥራዎች እንደሚያደርጉ መግለጻቸው ይታወሳል።

በዚህ መነሻ ኢንጂነር አይሻ መሃመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በሐድያ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በዞኑ የተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች አበረታችና ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ እንደሚሆኑ የገለጹት ሚኒስትሯ፣ የዞኑ ነዋሪዎች በሀገራዊ ለውጡ የተገኘውን ልማት ወደ ውጤት ለመቀየር እያደረገ ያለው ጥረት ስኬታማ ነው ብለዋል።

በዞኑ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ባለው በሌማት ትሩፋት፣ የግብርና ልማት ሥራዎች፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ ኢንቨስትመንት ዘርፍ አበረታች እንቅስቃሴ እንደሚታይባቸው ተናግረዋል።

በተለይም ሕዝብ በራሱ ተነሳሽነት የጤና ተቋማትን፣ መንገዶችንና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በመገንባት ለልማቱ መፋጠን እያደረገ ያለው ጥረት በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ኢንጂነር አይሻ ገልጸዋል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው የዞኑ ሕዝብ የመንግስትን ድጋፍ ሳይጠብቅ የተለያዩ መሰረተ ልማትና ሌሎች ልማት ስራዎች ለማከናወን እያደረገ ያለው ጥረት የሚያስደንቅ ነው ብለዋል።

በዞኑ የተሰራው ስራ አካባቢን በራስ ተነሳሽነት የማልማት ባህል ጠቃሚ በመሆኑ ለሁሉም አካባቢዎች ተሞክሮ የሚሆን ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ኢፋ ሙለታ በበኩላቸው መንግሥት ሁሉንም ዜጎች በማሳተፍ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማረጋገጥ የጀመረውን ሥራ የሚያጠናክር ተግባር  በመስክ ምልከታ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው ማህበረሰብ ድህነትን ለማሸነፍ የተያዘውን አቅጣጫ ለመደገፍ እየተሰራ ያለው ሥራ እንዲያጠናከሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ በርጋ በበኩላቸው በዞኑ በመስክ ምልከታው ህዝብ ያለውን አቅም ተጠቅሞ ልማትን ለማፋጠን እያደረገ ያለውን ጥረት መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ሀገራችን በልዩ ትኩረት እያካሄደች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በመረዳት ከተከላው እስከ እንክብካቤ ድረስ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው የነቃ ተሳትፎ የሚያስደስት ነው ብለዋል።

ዞኑን የጎበኙት ከፍተኛ አመራሮች ትናንት ከዞኑ አመራሮች ጋር መምከራቸው ይታወሳል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም