ቀጥታ፡

የኢትዮ-ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብር እየተጠናከረ መጥቷል - አምባሳደር ዶክተር ገበየሁ ጋንጋ

አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2015(ኢዜአ)  የኢትዮጵያና ቻይና ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው ወዳጅነት በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብር እየተጠናከረ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስያና ፓስፊክ አገራት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዶክተር ገበየሁ ጋንጋ ተናገሩ። 

በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የፕሮጀክት ማስተባበሪያና አጋርነት ቢሮ ኃላፊ መላኩ ሙሉዓለም በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተጻፈው በኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነት ትኩረት ያደረገው መጽሃፍ ለምርቃት በቅቷል።

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ ቻይና ኤምባሲ የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራንና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስያና ፓስፊክ አገራት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዶክተር ገበየሁ ጋንጋ፤ ኢትዮጵያና ቻይና ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ አገራት ናቸው ብለዋል።

አገራቱም ከቀደምት ሥልጣኔያቸው የወረሱትን ዘርፈ ብዙ አጋርነት በማስቀጠል በትብብር ላይ የተመሰረተ አጋርነታቸውን እያስቀጠሉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገኦ፤ ቻይና ምጣኔ ሃብታዊ እድገቷን ማጎልበት በጀመረች ማግስት ለበርካታ የአፍሪካ ታዳጊ አገራት ድጋፍ አድርጋለች ብለዋል።


 

በአሁኑ ወቅት እያካሄደች የምትገኘው በትብብር ላይ የተመሰረተ የልማት አጋርነትም ለአፍሪካ እድገት ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ አማካሪ ሚኒስትር ሸን ቺንሚን ቻይና በምትከተለው የልማት ትብብር ማዕቀፍ የአፍሪካን ልማት እየደገፈች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

ቻይና ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላት በእኩልነት፣ በወዳጅነትና በትብብር ላይ የተመሰረተው አጋርነት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደሳለኝ አምባው የኢትዮ-ቻይና እና የአፍሪካ ቻይና ግንኙነትን የሚዳስሱ የፅሁፍ ሥራዎች በበቂ ደረጃ እንደሌሉ አንስተዋል።


 

ዛሬ ለምረቃ የበቃው መጽሐፍም ክፍተቱን ለመሙላት ጉልህ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የመጽሐፉ ደራሲ መላኩ ሙሉዓለም በዓለም አቀፍ ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና ድረ-ገፆች የአፍሪካ-ቻይናን፤ የኢትዮ-ቻይናን ግንኙነት የሚዳስሱ ገንቢ ፅሁፎች ሲያቀርቡ በመቆየታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

የተቋማቸው የውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት ተመራማሪዎችም ሙያዊ የጽሁፍ ሥራዎችን በማዘጋጀት ለትውልድ የሚጠቅም የዲፕሎማሲ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲቲዩት የፕሮጀክት ማስተባበሪያና አጋርነት ቢሮ ኃላፊና የመጽሃፉ ደራሲ መላኩ ሙሉዓለም በበኩላቸው መጽሃፉ የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት በስፋት ዳሷል ብለዋል። 

ያም ብቻ ሳይሆን የቻይና-አፍሪካ ታሪካዊ፣ አሁናዊና የቀጣይ አመላካች ሃሳቦችን በማካተት ለአፍሪካና ኢትዮጵያ የሚሰጡትን ትምህርት ለማካተት ጥረት መደረጉን ነው የጠቀሱት። 

"የአፍሪካ ቻይና ግንኙነት፤ የኢትዮጵያ ተሞክሮ "Africa-China Relations: Ethiopia as a case Study"  በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ በሰባት ምዕራፍ እና በ240 ገጽ ተቀንብቦ ለአንብቢያን ቀርቧል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም