ቀጥታ፡

አየር መንገዱ የካርበን ልቀትን በመቀነስና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ነው - ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርበን ልቀትን ለመቀነስና  የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን  የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

የአየር መንገዱ አመራሮችና ሠራተኞች ዛሬ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ተገኝተው አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።


 

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ አየር መንገዱ በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 100 ሺህ ችግኞችን ለመትከል አቅዶ እየሰራ ነው።

ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ማኅበር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2050 የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪው ወደ ከባቢ አየር የሚለቀውን የካርበን ልቀት ወደ ዜሮ የማውረድ ግብ አስቀምጧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም የማኅበሩ አባል በመሆኑ ዕቅዱን ለማሳካት የካርበን ልቀትን የሚቀንሱ የአውሮፕላን ሞተሮችን መጠቀምና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

በዘርፉ የአየር ብክለትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በመደገፍና እንዲጠናከር በማድረግ አየር መንገዱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም የአየር ብክለትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።


 

ይህንንም ተከትሎ አየር መንገዱ ችግኞችን በመትከልም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ሰፊ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

የተቋሙ ሠራተኞች በበኩላቸው፤  የተተከሉትን ችግኞች በመንከባከብ ኃላፊነታቸውን እንዲሚወጡም በዚሁ ጊዜ ጠቁመዋል።

በቀጣይም በመላው አገሪቱ ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የአየር መንገዱ ሠራተኛ ማኅበር ፕሬዝዳንት ኪያ ለማ በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከሚወጣባቸው ተግባራት መካከል ችግኞችን መትከል አንዱ ነው።

በተለይም በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በርካታ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ  የተተከሉትን የመንከባከብ ሥራ በስፋት እንደሚሰራ ጠቁመዋል። 

የአየር መንገዱ የበረራ አስተናጋጅ ክርስቲያን ግዴለው በበኩሏ፤ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብም የሚያስደስት ተግባር እንደሆነ ነው የተናገረችው።  

በመጪው ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል መታቀዱ  ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም