የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የአረንጓዴ አሻራና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በድሬዳዋ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የአረንጓዴ አሻራና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በድሬዳዋ ጀመረ
ድሬደዋ ሐምሌ 8/ 2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በዘንድሮ የክረምት ወራት የሚያከናውነውን የአረንጓዴ አሻራ ልማትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መረሃ ግብር ዛሬ በድሬዳዋ ጀመረ።
ለመረሃ ግብሩ ማስፈጸሚያ 132 ሚሊዮን ብር መመደቡን ድርጅቱ አስታውቋል።
በተጨማሪ ድርጅቱ ከድሬዳዋ ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ከ15 እስከ 20ሚሊዮን ብር በጀት የተመደበለት የአፀደ ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነስርአት አካሂዷል።

በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የወደብና ተርሚናል ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ምህረተአብ ተክሉ መረሃ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መነሻ ሃሳብ የተጀመረውና ባለፉት አራት ዓመታት የተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ልማት የአለምን ትኩረት የሳበ ድንቅ ውጤት አስገኝቷል።
ይህ ውጤት በአለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ፣ በውጪና ገቢ ንግድ የባህር እንቅስቃሴዎች ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ማገዙን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባህር ላይ መርከቦች በተሳለጠ ንፍቀ ክበብ ያለ ተፅዕኖ እንዲጓዙ በማድረግ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ብለዋል።
በተጨማሪ ባለፉት ዓመታት የድርጅቱ ቅርንጫፎች በሚገኙባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ፤ በችግረኞች ቤት ዕድሳትና ግንባታ፤ በአፀደ ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ላይ ከልማት አጋሮች ጋር በመቀናጀት ያከናወናቸው ስራዎችንም ጠቅሰዋል።
ይህም የህፃናት የትምህርት ጥያቄዎች ለመመለስና የችግረኞችንም ኑሮ ለማሻሻል ወሳኝ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል።
ለተመሳሳይ ስራዎች ማስፈጸሚያ ዘንድሮ 132 ሚሊዮን ብር መመደቡን አመልክተው፤ በዚህም የድርጅቱ ቅርንጫፎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለመፈፀም ከመቶ ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን መትከል አንድ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መረሃ ግብር በድሬዳዋ አስተዳደር ልዩ ትኩረት ማድረጉን የጠቀሱት አቶ ምህረተአብ፤ ዛሬ የድሬደዋ ደረቅ ወደብና ተርሚናል አካባቢ መጀመሩ የዚሁ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
በድሬዳዋ ከችግኞች መትከል በተጨማሪ ከትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ብር በጀት የተመደበለት የአፀደ ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።
ግንባታው በሶስት ወራት ተጠናቆ ለመጪው ዓመት የመማር ማስተማር ስራ እንደሚዘጋጅ አቶ ምህረተአብ ገልጸዋል።
የሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራና የትምህርት ቤቶች ግንባታዎች ከትግራይ ክልል ጀምሮ ድርጅቱ በሚገኝባቸው የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሀመድ በበኩላቸው ፤ በትምህርት ላይ ተቀናጅቶ ሃብትንና ዕውቀትን ማዋል መጪዋን የዕድገት ባለቤት ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ድርጅቱ በድሬዳዋ የሚታየውን ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት ትኩረት ማድረጉ ትክክለኛ መሆኑን ተናግረዋል።