ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና በትግራይ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በውይይት ሊፈታ ይገባል

አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና በትግራይ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በውይይት ሊፈታ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አሳሰበ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥር በትግራይ ክልል ባሉ አህጉረ ስብከቶች ወቅታዊ የግንኙነት ሁኔታ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ምክትል ጠቅላይ ጸሐፊ ሓጂ መስዑድ አደም በሰጡት መግለጫ፤ በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት ተወግዶ በአካባቢው የሰላም አየር መንፈስ መጀመሩ መልካም ጅማሮ መሆኑንና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልፀዋል።


 

ጦርነቱን ተከትሎ በቤተክርስቲያኗና በትግራይ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከቶች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታትና እርቀ ሰላም ለማድረግ ከሰሞኑ የቤተክርስቲያኒቱ ፓትሪያርክን ጨምሮ አበው ሊቃነ-ጳጳሳትና የሰላም ልዑካን ወደ ትግራይ ማቅናታቸውን አስታውሰዋል።

የሰላም ልዑኩ ይዞት የተነሳው ዓላማ ሳያሳካ ወደ አዲስ አበባ መመለሱንና ይህም በመሆኑ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ አባቶችን ማሳሰቡን ተናግረዋል።

በዚህም በትግራይ ክልል የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አህጉረ ስብከቶች ከማዕከላዊው የቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር ጋር አስተዳደራዊና መንፈሳዊ ግንኙነታቸውን ማቋረጣቸውን እና ክልላዊ መዋቅር እያደራጁ እንደሆነ ሲገለጽ መቆየቱን ጠቁመዋል።


 

የጉባዔው የበላይ አባቶች በጉዳዩ ላይ በስፋትና በጥልቀት መወያየቱን ገልጸው፤ የተፈጠሩት ችግሮች በግልጽ በውይይትና በመነጋገር እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

የመነጋገርና የመደራደር አማራጭን ዝግ በማድረግ የተወሰደው አቋም ከቤተክርስቲያን መሠረታዊ አስተምህሮ ጋር የሚቃረን በመሆኑ በቤተ-ክርስቲያኒቱ አንድነት ላይ የሚኖረው ውጤትም መልካም ባለመሆኑ በሮች ሁሉ ለውይይትና ለንግግር ክፍት እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የፌደራልና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለሰላም የወሰዱት አቋም የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ የሕዝብ ለሕዝብና የተቋማት ግንኙነት እንዲጠናከር ተገቢውን ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በተለይም በቤተ-ክርስቲያኗ የተፈጠረው አለመግባባት በዘላቂነት ለመፍታት ንግግርና ውይይት እንዲቀድም በማድረግ የቤተክርስቲያንን አንድነት በማስጠበቅ ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች እንዲሁም በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰሩ ሁሉ የተፈጠረውን ክፍተት ሰላማዊ በሆነ አግባብ እንዲፈታ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነትን ለማስጠበቅ የተጀመረው ጥረት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ለሰላምና ለቤተክርስቲያን አንድነት የሚደረገውን ጥረት ሁሉ ጉባዔው እንደሚደግፈው ጠቁመዋል።

ሕብረተሰቡ በማንኛውም መልኩ የሚፈጠሩ አገራዊ አለመግባባቶች ሁሉ እንደ አገር የሚያመጣው አሉታዊ ጫና በመገንዘብ ሰላምንና አንድነትን በማስጠበቅ ሂደት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችና አገልጋዮች የአገር አንድነትና ሰላም እንዲጠበቅ ተግተው እንዲጸልዩና ምዕመናንን ሊያስተምሩ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም