ቀጥታ፡

በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለአገራዊ ፕሮጀክቶች እና ወቅታዊ ጥሪዎች ከ16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርገዋል - የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት

አዲስ አበባ ሐምሌ 8/2015 (ኢዜአ)፦በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በ2015 በጀት ዓመት ለአገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች ከ16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ እና የአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።

ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ ልማት እና እድገት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል።

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ(ዶ/ር) የተመራ ልዑካን ቡድን በዳያስፖራ ዲፕሎማሲና ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ላይ በዋሺንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ ላይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ፣የሚሲዮኑ ምክትል መሪ አምባሳደር ዘላለም ብርሃን፣ የሚሲዮኑ የዳያስፖራ ዲፕሎማቶች እና የኤምባሲው ሰራተኞች ተገኝተዋል።

በኤምባሲው የተከናወኑ የፖለቲካ፣የቢዝነስ ዲፕሎማሲ እና የዳያስፖራ ዲፕሎማሲና ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በ2015 በጀት ዓመት ለአገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች ከ16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ(ዶ/ር) ጠቁመዋል።

በግጭት ምክንያት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና የወደሙ መሰረተ-ልማቶችን መልሶ ለመገንባት፣ ለአገራዊ ጥሪ፣ ለገበታ ለትውልድ ፕሮጀከት፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ለበጎ አድራጎት ስራዎች ከ965 ሺ ዶላር በላይ በጥሬ ገንዘብ እንዲሁም ከ15 ሚሊየን ዶላር በላይ የአይነት ድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል።

14 የጤና እና የትምህርት ተቋማት መልሶ ግንባታም በዳያስፖራው ድጋፍ መጀመሩን አመልክተዋል።

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ እስከ ግንቦት/2015 ከሰሜን አሜሪካ ብቻ ግለሰቦች ከ483 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ወደ አገር ቤት(ሬሚታንስ)መላካቸውንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያመለከቱት።

ከድጋፉ በተጨማሪ በዳያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ረገድም መልካም ስራዎች መከወናቸው በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሁለንተንዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም