የፖሊስ መኮንኖች ሙያዊ ሥነ-ምግባር በመላበስ እየተወጡ ያለውን አገራዊ ኃላፊነት አጠናክረው መቀጠል አለባቸው- የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
የፖሊስ መኮንኖች ሙያዊ ሥነ-ምግባር በመላበስ እየተወጡ ያለውን አገራዊ ኃላፊነት አጠናክረው መቀጠል አለባቸው- የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2015(ኢዜአ) የፖሊስ መኮንኖች ሙያዊ ሥነ-ምግባር በመላበስ እየተወጡ ያለውን አገራዊ ኃላፊነት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች ያሰለጠናቸውን የፖሊስ መኮንኖች በዛሬው እለት አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች ተገኝተዋል።
ሰልጣኞቹ በፖሊስ ሳይንስ፣ በሥነ-ወንጀልና ወንጀል ፍትሕ፣ እንዲሁም በፖሊስ መኮንንነት ዘርፍ ከሰርተፊኬት እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ መቆየታቸው ተገልጿል።
ከተመራቂዎቹ መካከል በሰላምና ደኅንነት እንዲሁም በአስተዳደር ሥራ አመራር የተመረቁት ሰልጣኞች ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለተኛ ዲግሪ ያስመረቃቸው ናቸው።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፤ የፖሊስ መኮንኖቹ ፖሊሳዊ ሥልጠናውን በጽናትና ቁርጠኝነት ተቋቁመው ለምረቃ በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
የፖሊስ መኮንኖች የቀሰሙትን እውቀት ከክህሎት ጋር በማዋሃድ የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመሆኑም የሕዝብና የአገር ሰላምና ደኅንነትን በማስጠበቅ ሙስናን፣ ወንጀልን እና ጽንፈኝነትን በመዋጋት ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያውያንን ያለ አድሎ በፍፁም ቅንነት እንዲያገለግሉና ሙያዊ ሥነ-ምግባር በመላበስ የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ አሳስበዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት የወቅቱ ፕሬዝዳንትና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ በለውጡ መንግሥት ለጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ትኩረት ተሰጥቶ የሪፎርም ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አንስተዋል።
በዚህም የፌደራል ፖሊስ በሪፎርም ሥራው፤ ዘመን ተሻጋሪ ለሙያና ለሕግ ተገዢ የሆነ የሕዝብ አገልጋይ የፖሊስ አመራርና አባል ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ተቋማዊ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ለመገንባት የሚያስችል የሰው ኃይል ግንባታ ሪፎርም ሥራ መካሄዱን ገልፀው ቀጣይነት ያለው የሰው ኃይል ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር መስፍን አበበ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት ግንባታ ዩኒቨርሲቲ ተልዕኮውን እየተወጣ ዛሬ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የፌደራልና የመላው አገሪቱን የፖሊስ ሠራዊት የተማረና የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት የማሟላት ተልዕኮውን እየተወጣ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ዛሬ ለምረቃ የበቁ የፖሊስ መኮንኖች የሰነቁትን የፖሊስ ሙያና ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣት በመልካም ሥነ-ምግባርና ተቋማዊ እሴት እንዲወጡ አሳስበዋል።
ከተመራቂ ፖሊስ መኮንኖች መካከል ምክትል ኮማንደር ናስር ሙሳ የተጣለበትን ፖሊሳዊ ኃላፊነት በሙያዊ ሥነ-ምግባር ለመወጣት ያለውን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ተናግሯል።
ረዳት ኢንስፔክተር ውብሸት አበበ በበኩሉ፤ የሕዝብንና የአገርን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
ሌላኛዋ ተመራቂ ረዳት ኢንስፔክተር ሰብለ ሰዒድ በበኩሏ፤ በዩኒቨርሲቲው የቀሰመችውን እውቀትና ክህሎት ሙያዊ ሥነ-ምግባር በመላበስ የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት እንደምትወጣ ተናግራለች።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በ30 ሚሊየን ብር ወጪ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ያስገነባው የ5 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ በፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተመርቋል።