ቀጥታ፡

የጋምቤላ ክልል የተፈጥሮ ሀብት በማልማት የሕዝቡን ሕይወት ለመለወጥ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል- የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች

ጋምቤላ ሐምሌ 8/2015(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በማልማት የሕዝቡን ሕይወት ለመለወጥ አመራሩ አበክሮ መስራት እንዳለበት የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።

በክልሉ የተሰማራው የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የድጋፍና የክትትል ቡድን ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን የጀመረው የልማት ስራዎች  ጉብኝት ዛሬም እንደቀጠለ ነው። 


 

የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ንጉሱ ምትኩ የጋምቤላ ክልል እምቅ የውሃ፣ የመሬት፣ ምቹ የአየር ፀባይ እና የሰው ኃይል ያለበት  ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ በክልሉ ያለውን ፀጋ ወደ ልማት በመለወጥ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ጅምር ስራዎች ቢኖሩም በቂ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። 

ሀብቱን  ማልማት ከተቻለ የአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ጭምር ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ይህንም እውን ለማድረግ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ በክልሉ ያለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በማልማት የሕዝቡን ኑሮ ለመለወጥና የታሰበውን የብልጽግና ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ አመራሩ በቁጭት መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።


 

የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው ክልሉ የውሃ፣ የመሬት፣ የዓሳ ፣የማር፣ የእንስሳትና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶችን ከሌሎች አካባቢዎች በተለዩ ሁኔታ አቅፎ የያዘ ነው ሲሉ ገልጸዋል።


 

ሃብቶች እያሉ የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ ብዙ ያልተለወጠበት ሁኔታ መኖሩንና ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት አመራሩ አበክሮ መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በለውጡ የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በክልሉ ያለውን ሀብት በማልማት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በቀጣይም በአመራሩ የተሰጡትን ምክረ ሃሳቦች በመውሰድ የተሻሉ ውጤቶችን ለማስመዝገብ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም