ቀጥታ፡

የኦዲት ስራ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የማደራጀት ስራ በመከናወን ላይ ነው - የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት

ቦንጋ  ሐምሌ 08/2015(ኢዜአ):- የኦዲት ስራ ዓለም  አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የማደራጀት ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ ገለጹ።

የፌዴራልና የክልል እና የከተማ አስተዳደር ኦዲተሮች 22ኛው ዓመታዊ ጉባኤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ  እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው ላይ የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ዋና ኦዲተሮች ተገኝተዋል።

በፌደራል፣ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ያለው የኦዲት ሥራ እየተሻሻለ መምጣቱን ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ ገልጸዋል።

የኦዲት ስራውንም ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን  ጠብቆ እንዲከናወን በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል እየተደራጀ  መሆኑን አስታውቀዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች የኦዲት ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫና የአቅም ማጎልበቻ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳዳር ዶክተር ኢንጂነር  ነጋሽ ዋጌሾ  የክልሉ ዋና ኦዲተር የመንግስትና የሕዝብ ሀብት፣ ንብረትና በጀት ለታለመለት አላማ  ለማዋል  እየሰራ ነው ብለዋል።


 

በሂደት በሚገጥሙ የአሰራር ግድፈቶች ላይ የእርምት እርምጃ ለመውሰድም ሆነ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ  ጠንካራ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ከክልሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እና  አግባብ ካላቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ጥረት በርካታ ሀብትና ንብረትን ከምዝበራ ማዳን እንደተቻለ እና በርካቶች በሕግ ተጠያቂ ማድረግ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለተገኙ ውጤቶች ምክንያት በክልሉ ጠንካራ የኦዲት መስሪያ ቤት መገንባቱ እንደሆነ ጠቅሰው ተቋሙን ለማጠናከር ክልሉ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትም ተቋሙን ለመደገፍና ለማጠናከር  ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ በበኩላቸው የክልሉ ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ነጻና ጠንካራ ተቋም ሆኖ ስራውን እንዲያከናውን ክልሉ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።

ውስን  የመንግስትና የሕዝብ ሀብት ለተፈለገው ስራ ብቻ በትክክል እንዲውል ለማስቻል በተደረገው እንቅስቃሴ ጥሩ ውጤት መገኘቱንም ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም