የጉራጌ ዞንን ከስልጤና ከሃድያ ዞኖች የሚያገናኘውን የአስፋልት መንገድ ስራ በሦስት ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጉራጌ ዞንን ከስልጤና ከሃድያ ዞኖች የሚያገናኘውን የአስፋልት መንገድ ስራ በሦስት ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2015(ኢዜአ)፡- የጉራጌ ዞንን ከስልጤና ሀድያ ዞኖች የሚያገናኘው የአጣጥ ማዞሪያ ጉንችሬ ቆሴ ጌጃ ሌራ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ሥራ በሦስት ዓመት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለጸ።
ፕሮጀክቱ በአገርበቀሉ አለማየሁ ከተማ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭና በአይዲኮን ኢንፍራስትራክቸር ዴቨሎፕመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አማካሪ ድርጅቶች አማካኝነት እየተካሄደ ይገኛል።
የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቱ የጉራጌ ዞንን ከስልጤና ሃድያ ዞኖች በማገናኘት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማሳደግ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የቡታጅራ አካባቢ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ገዛኸኝ ዋቅቶሌ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ 97 ኪሎ ሜትር ርቀትን ይሸፍናል ብለዋል።
ለፕሮጀክቱ ከ5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ የሆነ ገንዘብ በመንግሥት ተመድቦለት ግንባታው በዚሀ ዓመት ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በግንባታ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን መፍትሔ ለመስጠት ከማኅበረሰብና ከአስተዳደር አካላት ጋር ምክክር በማድረግ ሥራውን ለማስቀጠል መቻሉን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ፣ ጥራትና በጀት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የአለማየሁ ከተማ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አይናለም ፈቃዱ፤ ፕሮጀክቱ በቻይና መንገድ ሥራ ተቋራጭ ሲካሄድ የቆየ ቢሆንም በተቀመጠለት ጊዜ ለማጠናቀቅ አልተቻለም ነበር ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የግንባታ ሥራውን በሦስት ዓመት ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚያስችል የጥሬ ዕቃና ማሽኖችን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁሶችን በተደራጀ መንገድ ለማቅረብ መቻሉን ጠቅሰዋል።
የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቱ የጉራጌ ዞን፣ ሃድያና ስልጤ ዞኖችን በማገናኘት የአካባቢውን ማኅበረሰብ የንግድ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረውም ነው የተናገሩት።
የጉንችሬ ከተማ ነዋሪው አቶ ዓባይነህ አምሳል እንዳሉት፤ የመንገድ ግንባታው መጓተት በአካባቢው ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድር ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት የግንባታ ሥራው በተሻለ መነቃቃት እየተከናወነ በመሆኑ ማኅበረሰቡን ሲያጋጥሙ የነበሩ የትራንስፖርት አገልግሎት የተሻለ እንደሚያደርገው እምነታቸውን ገልፀዋል።
የአጣጥ ማዞሪያ አካባቢ ነዋሪ ሸምሱ ታደምጋ በበኩላቸው፤ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ይገልጻሉ።
መንገዱ አጣጥ፣ ጉንችሬ፣ ዲንቁላ እና ጊጃ ቀበሌዎችን የሚያገናኝ ሲሆን፤ በወተራ፣ ተርሆኘ፣ ተረዳ፣ ጉንችሬ መገንጠያ፣ ጉስባጃይ፣ ወይራ፣ ሚቄ፣ ቆሴ እና ሌራ ከተሞች የሚያልፍ መሆኑ ተገልጿል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የጉራጌ፣ ሃድያና ስልጤ ዞኖችን በማገናኘት በዞኖቹ የሚገኘውን የግብርና፣ የቱሪዝም እና ሌሎች ጸጋዎችን ማኅበረሰቡ የሚጠቀምበትን ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር እንደሆነም ተነግሯል።