5ኛው የአፍሪካ ኅብረት የግማሽ ዓመት ስብሰባ በኬንያ ናይሮቢ በነገው ዕለት ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
5ኛው የአፍሪካ ኅብረት የግማሽ ዓመት ስብሰባ በኬንያ ናይሮቢ በነገው ዕለት ይካሄዳል
አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2015(ኢዜአ)፡- 5ኛው የአፍሪካ ኅብረትና በአፍሪካ የሚገኙ አካባቢያዊ የኢኮኖሚ ተቋማት የግማሽ ዓመት ስብሰባ በኬንያ ናይሮቢ ነገ ይጀመራል።
እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2017 በአፍሪካ ኅብረት የተደረገውን ሪፎርም ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት በዓመት ሁለት ጊዜ የሚያካሂደው መደበኛ ስብሰባ አንድ ጊዜ ብቻ እንዲካሄድና አንደ አስፈላጊነቱ አስቸኳይ ስብብሰባ እንዲጠራ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያን ጨምሮ በየዓመቱ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚካሄደው በሐምሌ ወር የኅብረቱ የመሪዎች የግማሽ ዓመት ስብሰባ እንዲታጠፍና በምትኩ የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች አካባቢያዊ ተቋማት የጋራ ስብሰባ እንዲያካሂዱ ተወስኗል።
በየዓመቱ ሐምሌ ወር ላይ የሚካሄደው ይኸው የጋራ ስብሰባው በዋነኝነት የአህጉሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውህደት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ በኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
በአፍሪካ ኅብረት፣ በአካባቢያዊ የኢኮኖሚ ተቋማት እንዲሁም በአባል አገራት መካከል ውጤታማ ትብብርና የሰው ኃይል ስብጥር ለመፍጠር የተደረሱ ሥምምነቶችና ሕጋዊ ማዕቀፎች አተገባበር እንዲገመግምም አቅጣጫ ተቀምጦለታል።
በዚህም መሰረት የዘንድሮ የግማሽ ዓመት የአፍሪካ ኅብረትና የአካባቢያዊ ተቋማት ስብሰባ ነገ “የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ማፋጠን” በሚለው የዘንድሮ የኅብረቱ መሪ ሀሳብ በኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ ይካሄዳል።
ስብሰባው በዋነኝነት በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማትና ሌሎች የአካባቢው ተቋማት ሊቀ-መንበሮች በአፍሪካ አሁን ያለውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውህደት የሚያቀርቡትን ሪፖርት በተመለከተ ውይይት ያደርጋል።
ጎን ለጎንም ስብሰባው በአፍሪካ ኅብረትና በአካባቢያዊ ተቋማት እንዲሁም በአባል አገራት መካከል በአንዳንድ ሴክተሮች ውስጥ ወጥ የሆነ የሰው ሃይል ድልድልና ስብጥር ለመፍጠር የሚያስችል ሥርዓት እንዲኖር ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይገመታል።
የአፍሪካን ውህደት ለማፋጠን እክል የሚፈጥረውን የአየር ንብረት ለውጥ በመከላከል፣ ተፈጥሯዊ ሃብትን በዘላቂነት ማልማትና መጠቀም እንዲሁም የአፍሪካ ልማት ባንክ አህጉራዊ ኢኒሼቲቮቹን በተመለከተ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ትላንትና ከትላንት በስትያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት መደበኛው የኅብረቱ 43ኛው የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በናይሮቢ መካሄዱ ይታወሳል።