ቀጥታ፡

የኢንሹራንስ ዘርፉን ችግር ፈቺ በሆኑ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች በመደገፍ ተደራሽነቱን ይበልጥ ማስፋት እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ ሐምሌ 7/2015(ኢዜአ)፦ የኢንሹራንስ ዘርፉን ችግር ፈቺ በሆኑ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች በመደገፍ ተደራሽነቱን ይበልጥ ማስፋት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ፋይናንስ አገልግሎት ማስፋት (ኤፍ ኤስ ዲ ኢትዮጵያ) እና የአፍሪካ ፋይናንስ አገልግሎት ማስፋት (ኤፍ ኤስ ዲ አፍሪካ) የተሰኙ ድርጅቶች በጋራ ያዘጋጁት የልምድ ልውውጥ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

መድረኩ በዋናነት የኢንሹራንስ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ሰለሞን ደስታ በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ ለኢንሹራንስ ዘርፍ እድገት ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ዘርፉን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ያሉ እድሎችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ ፈጠራን በማበረታታት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት፣ የእውቀት ሽግግር እና የኢኖቬሽን ልምምድን ማስፋት ይገባል ነው ያሉት።

የኤፍ ኤስ ዲ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤርሚያስ እሸቱ በበኩላቸው ድርጅታቸው በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ባለድርሻ ተቋማት ጋር በመሆን የፋይናንስ አካታችነት፣ የካፒታል ተደራሽነት እና አየር ንብረት ፋይናንስ ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በኢንሹራንስ ዘርፉ ላይ ፈጠራን በማበረታታት ሁለንተናዊ አሰራሮችን ለማጎልበት እንደሚሰራም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ዘርፉ በሚፈለገው ልክ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ለማሻሻል ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ባለድርሻ ተቋማት ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኤፍ ኤስ ዲ አፍሪካ የችግር ፈቺ ፈጠራዎች ዘርፍ ኃላፊ ኤሊያስ ኦሞንዲ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በኢንሹራንስ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን በችግር ፈቺ ፈጠራዎች በመታገዝ መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያን በዘርፉ የአፍሪካ ማዕከል ማድረግ አንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

በኢንሹራንስ ዘርፍ የካበተ ልምድ ያላቸው አቶ አሰግድ ገብረመድህን በበኩላቸው የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ዘርፍ ባስቆጠረው እድሜ ልክ አለማደጉን ተናግረዋል።

መንግስት የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ያስቀመጠው አቅጣጫ የኢንሹራንስ ዘርፉን እንደሚያነቃቃው ተናግረዋል፡፡

ተደራሽነት በማስፋትና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኢንሹራንስ ትምህርት በስፋት በመስጠት ዘርፉን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም