ለበጎ ፈቃድ አገልግሎትና ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል- አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር - ኢዜአ አማርኛ
ለበጎ ፈቃድ አገልግሎትና ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል- አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር
ደሴ ሐምሌ 7/2015 (ኢዜአ):- በክረምት ለሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት በብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተባባሪ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር ገለጹ።
በአምባሳደር ሀሰን የተመራ የከፍተኛ አመራር ቡድን በደሴ ከተማ የክረምት የበጎ ፍቃድ ስራዎችን ዛሬ አስጀምሯል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሕብረተሰቡን ችግር በተጨባጭ እያቃለለ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አምባሳደር ሀሰን ገልጸዋል።
ሕዝብን በማስተባበር የሚከናወኑ የክረምት የልማት ስራዎች ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ሁሉም ዜጋ ችግኝ በመትከል አሻራውን ከማሳረፍ ባለፈ የተከለውን ችግኝ ተንከባክቦ ማሳደግ እንዳለበትም አመልክተዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ቡድኑ ዛሬ ባስጀመረው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ከ80 ሺህ በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉ እና በአገልግሎቱም ከ79 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።
በአገልግሎቱ 80 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ተግባር ለማከናወን መታሰቡን ተናግረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተጠናከረ የመጣው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመንግስትን የልማት ክፍተት ከመሙላቱ ባሻገር የሕብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር እያቃለለ ነው ብለዋል።
የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብርም በከተማው የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል በሚያግዝ መልኩ በከተማው ዙሪያ ባሉ ተራሮችና በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚከናወንም ነው የገለጹት።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋሻው ተረፈ በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በ312 ሄክታር መሬት ላይ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ስራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
በመጪው ሐምሌ 10 በአንድ ጀምበር ከ400 ሺህ በላይ ችግኝ ለመትከል አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።