በ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ የሚተገበር አገር በቀል የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች የአቅም ግንባታ ድጋፍ መርሐ-ግብር ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ የሚተገበር አገር በቀል የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች የአቅም ግንባታ ድጋፍ መርሐ-ግብር ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ ሐምሌ 7/2015(ኢዜአ):- በ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ የሚተገበር አገር በቀል የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች የአቅም ግንባታ ድጋፍ መርሐ-ግብር ዛሬ ይፋ ሆኗል።
የሰላም ሚኒስቴር፣የጀርመን አግሮ አክሽን እና የራስ አገዝ አሰራር ድርጅቶች መርሐ-ግብሩን መተግበር የሚያስችላቸው የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል።
መርሐ-ግብሩ ለአምስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን 70 አገር በቀል ድርጅቶች ተካተውበታል።
የገንዘቡ ወጪ በአውሮፓ ሕብረት እና በጀርመን አግሮ አክሽን ግብረ ሰናይ ድርጅት እንደሚሸፈን ተገልጿል።
ኦሮሚያ፣አማራ፣አፋር እና ቤንሻልጉል ጉሙዝ መርሐ-ግብሩ የሚተገበርባቸው ክልሎች ናቸው።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር እና ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥ አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና የጎላ መሆኑንና በዚህ ረገድም መርሐ-ግብሩ ድርጅቶቹን በማበረታታት ዜጎች አካታች የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ብለዋል።
ከዚህ አኳያ መርሐ-ግብሩ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸው ለተግባራዊነቱ የሰላም ሚኒስቴር የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
የጀርመን አግሮ አክሽን ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ትርንጎ ክንፈ ገብርኤል በበኩላቸው ድርጅቱ ከአጋር ድርጅቶች እና ከመንግስት ጋር በመሆን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የአቅም ግንባታ ላይ በመስራት የሚጠበቀውን ሚና እንዲወጡ እንሰራለን ብለዋል።
በኢትዮጵያ የራስ አገዝ አሰራር ድርጅቶች ሕብረት ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ አካሉ የአገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን አቅም በማጎልበት ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደሚቻል ገልጸዋል።
መርሐ-ግብሩ አገር በቀል የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶችን በማብቃት፣ የዜጎችን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ለማሳደግ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።